ይድረስ ለጦማሬ

ይድረስ ለጦማሬ ለምወድሽ እነሆ የአንድ አመት ምስጋናዬን እንቺ ይህን ደብዳቤ የምፅፍልሽ ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ የነፃነቴ በር ነሽ ፡፡ እንደ ፍላጎቴ፣ ባሻኝ ሰዓት ክፍቼ ያሻኝን ያመንኩበትን እፅፍና አትሜ ምላሹን ባንቺው በር አገኘዋለሁ፡፡ ስለ ልማት ስለ እድገት ስለጥበብ ሥለ ሃይማኖት ስለ ብዙ ስለ…ዎች እፅፋለሁ፡፡ የት አትመዋለሁ? አታሚዬን አስከፋ ይሆን? በኤዲተሩ እይታ እምነቴ እንዴት ነው? ያትምልኛል ወይስ. . .? ይህ የእኔ ጭንቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኔ ጦማር አኝቺ አለሽለኝ፡፡ እንዳሰብኩት እንጂ ከቶ እንዳሰበው የሚደርግሽም የሚከፈትሽ የለም፡፡ የማምንበት እና የምፈልገውን አትምብሻለሁ፡፡ የበር ዘብ የለብሽም ከልቦናዬ በቀር ጠባቂ እና አውዳቂም አፅዳቂም የለብሽም፡፡ በውስጤ የፈላውን የመልካም እሳቤዎቼን ችግኝ እጄና ልቦናዬ አብረው ውዷ ጦማሬ ሆይ ባንቺ ማሳዬ ላይ ይዘሩታል፡፡ በቅሎም ፍሬውን አይቼዋለሁ፡፡ እናም ጦማሬ የልቤ መስኮት፡፡ የእምነቴ መንገድ፡፡ የአንድ አመት ምስጋናዬን እንሆ፡፡ ይህን ደብዳቤ እኔ ብፅፈውም ብዙ ጦማሪያን አንብበው እንደሚወዱልኝ ይሰማኛል፡፡ ምክንይቱም ይህን ስሜቴን ይጋሩኛልና፡፡

እነሆ በአዲስ ዘመን ላይ እገኛለን፡፡ በአዲስ የህይወት መስመር እና በአዳዲስ አማራጮችም ላይ ነን፡፡ ለአዲሱ ዘመንም አዲስ ቴክኖሎጂ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ አረማመድ፡፡ በዚህ በአዲስ ዘመንም፣ መዛኝ እና አዲሱን ዘመንም የሚመለከት አዳዲስ አስተሳሰቦችንም የሚቀበል በአዲሱ መንገድ ለመሄድ ዝግጁ የሆነ እይታ እና አመለካከትም ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም የምናራምድበት አዲስ ሚዲያ ያስፈልገናል፡፡ እነሆ የዘመን ስጦታዬ የኔ ጦማር የዚህ የአዲስ ሚዲያ ውጤት ነሽ:: የኔ ጦማር የምወድሽ የአዲሱ ዘመን ገፀ በረከቴ ነሽ፡፡ ከልካይ ፈቃጅ፣ አዛዥ ናዛዥ የለብንም ጦማሬ ሆይ፡፡ ፖለቲከኞች የፖለቲካው ምህዳር ጠበበ ይላሉ፡፡ ኑሮን መጋፋት፣ የኑሮን ተግደሮቶቹን መቋቋም ያቃታቸው ደግሞ የኑሮ ምህዳሩ ጠበበ ይላሉ፡፡ ጦማሬ እኔ እና አንቺ ግን ይህ ሁሉ አይመለከተንም፡፡ እጅግ በጣም ሰፊ እኔና አንቺ አቅማችን እስከ ፈቀደ የምንሮጥበት የአዲሱ ዘመን አዲስ መስክ አለን፡፡ የአዲሱ ዘመን ዳና – ፍኖተ ጦማር፡፡ እኔ እና ጦማሬ እንፋንናለን፤ የአዲሱ ዘመን፣ የአዲሱ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆነው አዲሱ ሚዲያ፡፡

መጦመርን ከአመት በፊት ስጀምረው ብዙም እውቀቱም አልነበረኝም፡፡ ወረቀት የፈጀሁባቸው ግጥሞቼን የማወጣበት መንገድ አፈላልግ ነበር፡፡ ግጥሞቼን ለማውጣት የሄድኩበትመንገድ ትልቅ ጉልበት እውቀት እና ትውቀት ይፈልግ ነበር፡፡ በትንሽ ጉልበቴ፣ በትንሽ እውቀቴ ትንሽ ለፍቼ ነበር፡፡ ግን አልተሳካልኝም፡፡ እናም ከአውደ ጦማር እጄን ይዞኝ የገባ አንድ ሰው አለ፡፡ “ትንሹ ቴስ” ጦማሬ ሆይ ይህን ሰው ማመስገን አለብሽ፡፡ ይህ ሰው ባይኖር ኑሮ እኮ ፍቅር ጦማሬ ሆይ እኔ እና አንቺ ተዋውቀን እስከ አሁን ያሳለፍንነውንም ፍቅር እና የወደፊቱንም አንመሰርተውም ነበር፡፡ እኔም ይህን ደብዳቤ አልፅፍልሽም ነበር፡፡ እናም ጦማሬ እንዳልክን እንዴት እንደምታመሰግኝው አላውቅም፡፡ እንዳልክ የመጠንሰሻሽ ገንቦ ብቻ አይደለም፤ እዚህም እድትደርሺ የመጥመቂያሽ ጋን፣ የመጠጫሽም ዋንጫ ነው፡፡ ጦማሬ ሆይ ገለታን እነሆኝ በይው፤ ከመቀመጫሽ ተነተሸ፣ እጅ ነስተሽ አመስግኝው፡፡ ወዳጃችን እንዳልክ እኔን እና የጦማሬ እናመሰግንሃለን፡፡

ውዷ ጦማሬ ሆይ እምነቴን ያሰፈርኩብሽ፡፡ እሳቤዎችን ያጋራሁብሽ፡፡ ብሶቴንም ጭንቀቴንም ንዴቴንም ትንፍስ የምልብሽ አንቺው ነሽ፡፡ ውድ ጦማሬ ሆይ የኔ እና የአንቺ ቁርኝት ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ለፅሁፍ ስራዎቼ መስኮት ከመሆንሽም በላይ እኔን ከሌሎች ጋር አስተዋውቀሽኛል፡፡ ሃሳባቸውን አነብ ዘንድ እኔንም ያነቡኝ ዘንድ አንቺው ምክንያት ሆነሽኛል፡፡

ጦማሬ ሆይ እወድሻለሁ፡፡

ርዕሱን ከስር

ቀና ብዬ ባይሽ

ጨረቃ የለሽም

እናም. . .

ሰማዩም ከፍቶታል

ፈገግታውን አጥቷል

ክዋክብቱም የሉም

ደመናት ከብደዋል

ጨፍግጓል ፀልመሟል

እኔም ውስጤን ከፋኝ

አቅንቼ አስግጌ ፍለጋዬ ጠፋኝ፡፡

ለካስ. . . ወቅታት ይዞራሉ

በዑደት ምህዋር

. . . . . . ይሽከረከራሉ

ይፈራረቃሉ

በማይቆም በማይሞት

ልውጠት ቁመት ዝንፈት

ላፍታ በሌለበት

በህዋው ህግጋት

እናም . . . . ኡደት ይቀጥላል

በማይቆመው ጅረት

ህይወት ይንፏለላል

ግልጠቱ ክስተቱ ውበቱ ድምቀቱ

ዘመኑን ጠብቆ ወዝ ቅባቱ አልቆ

ተገፍቶ ይወርዳል

ኡደት ይ. . . . ቀ. . . .ጥ. . . ላ . . . .ል. . . . .

መቆሚያም የለውም ሕይወትም ይነጉዳል

ቅኝት ምቱን ጠብቆ ይፈሳል ይፈሳል ይፈሳል ይፈሳል . . . . .

የማይቆም የማይሻር

የልደት የእድገት የውርዛት

ጎልምሶ የማርጀት

ከዚያም ደግሞ የህልፈት

ሰንሰለት ቆልፎ

ህይወት ቅኝቱ ነው መቆሚያ የለውም

ይፈሳል. . . . . ይፈሳል . . . . . ይፈሳል . . . . .

የፍጥረት  ህግ  ነው ዑደት ይቀጥላል

የማይቆም የማይሻር

የልደት የእድገት የውርዛት

ጎልምሶ የማርጀት

ከዚያም ደግሞ የህልፈት

ሰንሰለት ቆልፎ

ዑደቱ ነው ና ሕይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡

እናም. . . .  .

ሳስበው

ይከፋኛል

ሳስበው

እንደማልፍ

ሳውቀው

ስኳር ፣ስኳር ፣ስኳር….እንደገናም ስኳር

ልጅ እያለሁ ከማስታውሰው እና ከማውቀው ልጀምር፣ እቤታችን የቀበሌያች ቁጥር የተፃፈበት የቀበሌ የሸማቾች ካርድ ነበረን፡፡ በዚሁ ካርድም፣ በየወሩ ከቀበሌ በቤተሰባችን ቁጥር ልክ በኪሎም ሆነ በሊትር ከሚሰፈረው አንድ፣ አንድ እየለካ ወር ጠብቆ፣ አሰልፎ መንግስት የቀበሌው ነዋሪነታችንን ድርጎ ይሰጠን ነበር፡፡ እኔን ደስ የሚለኝ ግን ቀበሌ እናቴ ወይ ደግሞ እህቴ ይዘውኝ ሲሄዱ ሰልፍ እስኪደርስ ድረስ ከእድሜ እኩዮች ጋር የምጫወተው ጨዋታ ነው፡፡ ኳስ እንጫወታለን፣ ድብብቆሽ አባሮሽ፣ የቁም እርግጫ፤  ክረምት ሲመጣ ደግሞ ኳስ ጨዋታውን በብይ እንቀይር እና መጫወት ነው፡፡ አ. . .ቤ. . . ት. . .!!! ደስ ሲል፡፡ የማይጠገብ የልጅነት ጨዋታዬን፤ ምነው ሰልፉ ባይደርስ እያልኩ እጫውት ነበር፡፡ ከጨዋታዬ በተጨማሪም ወር መድረሱን እንድናፍቅ የሚያደርገኝ ደግሞ የቀበሌው ህብረት ሱቅ ሻጭ ያስለመደችን ጉርሻ ነበር፡፡ ሰልፈኛውን እየገረመመች አልፋ ወደ መሸጫ ሱቅ ትገባና ስራ ከመጀመርዋ በፊት ወይ ገንዘብ ተቀባይዋ ሂሳብ ተቀባላ  ሸማች ወደ እሷ እስከሚመጣ እኛን ታሰልፍ እና በርጥበት የጠጠረውን ስኳር ትሰጠን ነበር፡፡ እኛም ለእሷ ለየት ያለ ፍቅር ነበረን፡፡ ቤተሰቦቻችን ግን አይወዷትም ነበር፡፡ ሚዛን ትሸቅባለች፣ ታዳላለች ይላሉ፤ እኛ ግን እንወዳት ነበር፡፡ የቀበሌው ጣጣ አልቆ የተሰጠንን ስኳርም ሆነ ጨው ዘይትም ሆነ ሳሙና አንዱ ካንዱ እንዳይቀላቀል በአንሶላ ጨርቅ ወይ ደግሞ በከረጢት እንቆጣጥር እና በሳጠራ ዘንቢላችን ከተን ወደ ቤት ከእናቴ ወይ ከእህቴ ጋር፡፡

ታዲያ ይህ ከቀበሌ የሚመጣ ስኳር እና ዘይት ወር ሳይደርስ ሲያልቅ ሰፈር ውስጥ ካሉ የችርቻሮ ሱቆች እንገዛለን፡፡ የምላከውም ታዲያ እኔ የቤቱ ትንሽ ልጅ ነኝ፡፡ ተጠርቼ የዘይት ቡትሌ እና ሳንቲሟ እየተሰጠችኝ፣ ሰፈራችን ያለው ባለ ኪዮስክስ ስም እየተነገረኝ፣ ቶሎ ገዝተህ ና ስትመለስ የማድረግልህን አታውቀውም እባላለሁ፡፡ ምን እንደሚደረግልኝ ግን በደንብ አውቀዋለሁ፤ እናፍቀዋለሁ፡፡ ግን ሁልግዜም አታውቀውም እየባልኩ እላካለሁ፡፡ ሳንቲሜን እና የዘይት መግዣ ቡትልዬን ይዤ ወደ ተነገርኝ ሱቅ ብንንንንንንን- በሩጫ፡፡ ከቤትም ልላክ ለጎረቤት ወደዛች ኪዮስክ ሁል ግዜ በሰብበ አስባቡ እሄዳለሁ፤ ከቤት ስጦታዬ በተጨማሪ ባለሱቁ ያስለመደኝ የኮሾ ከረሜላ ጉርሻ ነበርኝ፡፡ የተላኩትን ቆጣጥሬ፣ ከረላሜላዬን በኪሴ ይዤ በሩጫ ወደቤት እመላሳለሁ፡፡ እቤትም፤ እናቴ ከወፍራም ምርቃት ጋር ቤት ያለውን አሹቅም ሆነ ቆሎ ወይም ዳቦ ትሰጠኛለች፡፡ የተሰጠኝን በኪሴ ይዤ ወደ ጨዋታ፡፡ ወደ ጨዋታ ከመሄዴ በፊት ግን ከግቢያችን ውስጥ ቆም ብዬ በአጥር ቀዳዳ አጮልቄ ከሰፈራችን ልጆች እነማን እንዳሉ አያለሁ፡፡ የቢጥም ጨዋታ የተዋዋሉኝ ልጆች ካሉ ቀድሜ ስማቸውን “. . . ባይጥም፣ . . . .ባይጥም” እላቸዋለሁ፡፡ ቀድመው ቢጥም ካሉኝ ግን  አካፍላቸዋለሁ፡፡ ያላሉኝን ግን  እንቁልጭልጭ  እያልኩ ከፊታቸው እበላለለሁ፡፡ ያቁለጨለጩኝም ካሉ በተራዬ አቁለጨልጫቸዋለሁ፡፡ እንዲየው ነገሩን እንጂ አንማረርም፡፡ ትንሽ ካቁለጨለጭኩዋቸው በኋላ ግን ለእነሱም እሰጣቸዋለሁ እየተጫወትን አብረን እንበላለን፡፡ አንጨካከንም የበላይነትን ለማስጠበቅ ያህል ግን ትንሽ ጎርደድ ጎርደድ እያልን የልጅነት ጉረራ እንጎርራለን፡፡ ከዛም ወደ ጨዋታችን እንመለሳለን፡፡ ይሄ የልጅነቴ ነው፡፡

ድምጤም ጎርንኖ፣ ፊቴ ጠጉር አብቅሎ እና ሰውነቴም ጎልምሶ ለህይወት ወግ ደረስኩና ስራ ስይዝ  የሆነውን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ ዘይት ከአስር እስከ አስራ ሁለት ተነስታ እጥፍጥፍ ብላ በሊትር ከሃያ አራት እስከ አርባ ስምት ብር ደርሳለች፡፡ ከዚህ ዋጋ በላይ ገበያ ውስጥ ስላለው የዘይት ዋጋ እኔን መሰሎቼን አይመለከተን፡፡ ባለጉዳይ ይጨነቅበት፡፡ ኦሆይ፣ እሱ ስለምን ይጨነቃል? “ላለው በሰማይ መንገድ አለው” አይደል የሚባለው? ለእኛ ግን የሃያ አራትዋ ገበያ ላይ ከተገኘች እሰየው ነው፡፡ የባለ ሃያ አራትዋ ብር ግን የማትገኝባቸው ግዜያት ይበዛል፡፡ ድንግት ስውር ትላለች፡፡ ከዛማ እንደ መስቀል ወፍ . . . ያው አሁንማ ለምደነዋል፡፡ ድሮ ልጅ እያለሁ፣ ወር ተጠብቆ ከቀበሌ የህብር ሱቆች ትገኝ የነበረችው ዘይት አሁን የጀሪካን ዳና እየተከተሉ ከችርቻሮ ሱቆች ወይ ዘይት ሲመቻት ወይ ነጋዴያኑ ሲመቻቸው ነው የምናገኛት፤ ተናፋቂዋን ዘይት፡፡

የችርቻሮ ሱቆች የመሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ የተተመነላቸውን የመሸጫ ጣሪያ ዋጋዎቻቸውን በሚታይ ቦታ እንዲለጥፉ በተደረገው መሰረት ከየሱቆቻቸው መስኮት እና በሮቻቸው ላይ ለጥፈዋል፡፡ ስኳር 14.50 ዘይት በለ ሶሰስት ሊትር 71 ብር ከምናምን ሳንቲም ዱቄት፣ የዱቄት ወተት፣ . . . በዚህ ሰሞን ዋጋቸው እንጂ አይነቶቹ የሉም፡፡ ከተገኙም በስንት ድካም ነው፡፡ ዘይት ከሌለች የለችም ስኳር ግን ከተገኘችም ከአንድ ኪሎ በላይ መግዛት አይቻልም ሻጩም በጄ አይል ከአንድ ኪሎ በላይ፡፡ “ለምን ብትሉት?” ምላሹ “ክልክል ነው፡፡” ነው መልሱ፡፡ ፍትሃዊ የስኳር ስርጭት እንዲኖር ታስቦ የተደረገ ይመስላል፡፡ ይሁን ይህም መልካም ነው፡፡ ግን አንዳንዴ ስኳርም የበላት ጅብ  አልጮህ ይላል፡፡ ታዲያ ይህን ግዜ

እኔ አልናገረው እኔ አልተነፍሰው

ስንት ነገር አለ ውስጤ ‘ሚላወሰው፣

እንዳለው አዝማሪው፡፡ ከቤት ስንት ነገር አለ፡፡ ወተት የሚፈልጉ ጨቅላ ሕፃናት ይኖራሉ፣ ስንት ጣፋጭ የለመዱ ልጆች ይኖራሉ፡፡ አረ ሚስቶችም አይጠፉ፤ ያኔ ህፃናት ወላጆቻቸው ላይ፣ ወላጆች ነጋዴያን ላይ፣ ነጋድያን መንግሰት ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ፡፡ መንግሰትስ ምኑ ሞኝ፤ መልሶ ጣቱን ስግብግብ ነጋድያን ላይ ይቀስራል፡፡ ተቀሳስሮ ኑሮ፡፡ ስኳር ግን የለም፡፡

መቀሳሰር ሲጀመርም፤ ቤታችን ያለው ቴሌቭዥንም መጋዘን ሙሉ ድርድር ስኳር ከጀርባ እያሳየን አንዱን ተመራጭ ሹም ከፊት አስቀድሞ፣ . . . የስራ ድረሻቸውን እና ኃለፊነታቸውን አስከትሎ በምሽት ዜና እወጃው ሃገሪቱ ውስጥ ምንም አይነት የስኳር እጥርት አለመኖሩን አስታወቁ ይለናል፡፡ እሺ ሲነጋስ? ሲነጋማ ሰኳር ላይኖር ይችላል ወይም ደግሞ ስኳር የለም፡፡

የስኳርን መጥፋ ተከትሎ ህዝብ ይጮሃል፡፡ የፈረደበት ጋዜጠኛ የህዝብን ብሶት ያሰማል፡፡ የችርቻሮ ሱቆችን ከኋላው ያደርግና አንዱን የሱቅ ባለቤት ወይ ሸማች ከፊት አስቀድሞ የስኳር እጥረቱ አለመቀረፉን ይዘግባል፡፡ ስኳር በገበያ ውስጥ የለም፡፡ የሸማቾችን እና የችርቻሮ ሱቅ ባለቤቶቸን በዋቢነት ያቀርባል፡፡ ስኳር የለም፡፡ እንደገና ሌላ ዘገባ ይሰራል፤ ይህው ጋዜጠኛ፡፡ በቀደም እለት ያሳየንን ተመራጭ ሹም ወይም ደግሞ ምክትላቸውን ዛሬም ከቴሌቭዥናችን መስኮት ብቅ ያደርግና፡፡ የቀረቡት ሰውየም፣ ምንም አይነት የስኳር የምርት እጥረት በሃገሪቱ ውስጥ እንደሌለ እና በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት የአቅርቦት እና የስርጭት ችግር እንደተከሰተ እና በቀጣይ ጥቂት ቀናት ስኳር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ እንደሚሰራጭ ይነግሩናል፡፡ ደስ ይለናል፡፡ አያይዘውም ይቀጥላሉ፣ መንግስት ችግሩን ለቅረፍም የቁጥጥር ስርዓት አዘጋጅቶ ችግሩን የፈጠሩትን ነጋዴዎችም የሚቀጡበት መንግድ ተግባራዊ ስላደረገ ህብሰተሰቡ ከመንግስት አካለት ጋር በመተባበር ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበው የዜና ዘገባው ያበቃል፡፡ ኑሮአችን እንዲህ ይቀጥላል፡፡ ለነገሩ በዚህ ሁኔታ የተማረረው ህብረተሰብም ስንት ጥቆማ አቅርቦ ጥቂት የማይባሉ ሱቆችን እንዳሳሸገ ይታወሳል፡፡ ችግሩ ግን ነጋድያን በቅጣት የሚማሩ አይነት አይደሉም፡፡

እሰይ ሰበር ዜና የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ በየዜና ዘገባው እንሰማለን፡፡ የስኳር ጠኔያችንን የሚያስታግሱ ፋብሪካዎች መንግስት በሰፊው ገባበት ብቻውንም እንደማይሆንለት ሲረዳ ፍላጎት እና አቅም ላላቸው ባላሃብቶች መስኩን ክፍት አደረገ፡፡ ፋብሪካዎቹ ግንባታቸው አልቆ ወደ ምርት ሲገቡ፣ እኛም እዚያ ዘመን ስንደርስ “የለም፣ ስኳር የለም” እንላለን፡፡ እስከዚያው ግን የልማት አሳላጭ ጋዜጠኞቻችምን በየዘገባዎቻቸው አሁን አሁን በሚያስብል ወኔ፣ ስሜታዊ ሆነው የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ሂደት እና ሲጠናቀቁም የሚትረፈረፈውን  የስኳር ምርትን በምናብ ያስቅሙናል፡፡ ይህም ተስፋ ነው፡፡

ዛሬ ግን፤ “ስኳር፣ ስኳር” የሚለውን ዘፈን ያለ ዜማ እያንጎራጎርን ነው፡፡ የሆነ ሰዓት በሰፈራችን የሚገኙት የችርቻሮ ሱቆች በሙሉ አዳርሼ ስኳር የለም፡፡ አንዱ ወደ አንዱ እየጠቆሙኝ እኔ ተስፋ ሳልቆርጥ ስዞር ከአንድ ሩህ ሩህ  ነጋዴ ሱቅ ውስጥ የማዳበሪያ ርጋፊ ስኳር አገኘሁ፡፡(የነጋዴ ሩህ ሩህ እምምምም፡፡) ግን ሩህ ሩህ ያስባለኝን ነገር ልንገራችሁ፡፡ ሩብ ኪሎ መዝኖ ሰጠኝ፡፡ ጨምርልኝ ብዬ ደለልኩት አልሆነልኝም፣ ለመንኩት አልሆነልኝም፣ ተቅለስልሼም ተለማምጬም ላግባባው ሞከርኩ እሱ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ያለችውን ለሁሉም ላዳርሳት በቃህ አለኝ፡፡ ሩህ ሩህ አይደል? ለኔ ይበቃኛል ሩብ ኪሎ ስኳሬን ይዤ “ቤቴ ጌጤ”ን እየዘፈንኩ ወደ ቤቴ፡፡ በቁጠባ ስኳሬን ተጠቀምኳት፤ አጣጣምኳት፡፡ ስጨርሳት “እንደገና፣ ስኳር እንደገና”ን እየንጎራጎርኩ፣ ስኳር ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ዛሬም ተመስገን ነው ስኳር የለም፡፡ አማርሬ የት ልደርስ?  ስኳር ባይኖርም ግን “ለ. . . ወረዳ ነዋሪዎች በሙሉ፣ በወረዳችን ምንም አይነት የስኳር እጥረት የሌለ መሆኑንተገንዝባችሁ ስኳር የለም የሚሏችሁን የወረዳውን ነጋዴዎች ለወረዳው ንግድ እና ኢንዱስትሪ በሚከተሉት ስልክ ቁጥሮች መጠቆም የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡” (የጠፋው ስኳር አፈላላጊ ኮሚቴ) እኔ ያልፃፍኳቸው ስልክ ቁጥሮቹ ከስር አሉ፡፡ በቅንፍ ያለችውን እኔ ማስታወቂያውን ለለጠፉት የሰጠኋቸው ስያሜ ነው፡፡ ታዲያ ተመስገን አይደለም እንዴ ቢያንስ ቅሬታ ሰሚ አቤት የምንልበት ተገኘ፡፡ እኔ የካላንደር ተንቀሳቃሽ እንዴት ልደውል ስልኬ የምትሞላበት ቀን ገና ነው፡፡ ምስጋና ለቴሌ (call me back) እባክህ ደውልልኝን ለጀመረው እና እባክህ ደውልልኝ አልኩ በተለጠፈው ቁጥር፤ ግን መልስ የለም፡፡ ሳንቲም ሞልቼ ደወልኩ ስልኩ አይነሳም፡፡ ሞከርኩ ስልኩ አይነሳም፡፡ ቅዳሜ ስለሆነ ይሆን? ልብ በሉልኝ የተለጠፉት ስልክ ቁጥሮች ግን የተንቀሳቃሽ (የሞባይል) ስልክ ቁጥሮች ናቸው፡፡ በማግስቱም በሰንበቱ ይሁን በመዝናናት ምክንያት ስልኪቱ መልስ አልነበራትም፡፡  ምናልባትም ሞባይሊቱ የቢሮ ሳትሆን አትቀርም፡፡ በሰንበት አትነሳም፡፡

ሰኞ መጣ በጠዋቱም የዞረ ድምር እና ድካም ይሁን በተደጋጋሚ ስደውልባት ጠዋት ላይ መልስ አልነበራትም፡፡ ቴሌ በቅርቡ አስቀርፆ መልስ እንድትሰጥ ያዘጋጃት ማሽን “ይቅርታ፣ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም፤ እባክዎ ትንሽ ቆይተው ይደውሉ፡፡” የሚል ድምፅ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በተደጋጋሚ ሲያስተናግደኝ ቆየ፡፡ ወደ ረፋዱ ግድም ግን ስልኩ ተነሳ፡፡ “ሀሎ” “ሀሎ” ተባባልን

“ሀሎ፣ እባክህ ባለ ሱቆች እኛ ሰፈር ስኳር የለም እያሉኝ ነው” አልኩት፡፡ “የት አካባቢ አለኝ?” ሰፈሬን ነገርኩት፡፡ “እንዴት?” አለኝ፡፡ “አልቋል አሉኝ፡፡”

“ታዲያማ አትጨርስ አይባል መጥቶ እንዲውስድ ንገረው፡፡ ስኳር የለም ካላለህ ምንም አይደለም እስኪወስድ ነው፡፡ ‘የለም’ ማለት ነው የማይቻለው” አለኝ “እሺ፡፡” አልኩና ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ “ከአንድ ኪሎ በላይ አልሰጥ ብሎኛል ምን ይሻለኛል?” አልኩ፡፡ “ማነው ያለህ?” አለኝ “ባለሱቁ” መለስኩ “እንዴት?” “እኔ ምንአውቃለሁ?” ከአንድ ኪሎ በላይ እንዳንሸጥ ታዘናል አለኝ” አልኩ ከጠያቂነት ወደ ተጠያቂነት ዞርኩ፡፡ “አገናኘኝ አለኝ፡፡” በሰአቱ እሱቁ አካባቢ ስላልነበርኩ ባለሱቁን ላገናኘው እንደማልችል ነገርኩት፡፡ “በል ሱቅ አካባቢ ስትሄድ እንድታገናኘኝ አለኝ፡፡” እሺ ብዬ ስልኬን ዘጋሁ ከቆይታ በኋላ ሱቅ ሄድኩ፡፡ አሁን የምሄደው ስኳር ልገዛ አይደለም ለዚህች ፅሁፍ ፍጆታ የማውላትን መረጃ ፍለጋ ነው፡፡

“ባለ ሱቅ፣ ስኳር አለ?” “አለ” አለኝ

“አምስት ኪሎ ስጠኝ” አልኩት እንደማይሰጠኝ ልቦናዬ ያውቀዋል ግን ጠየቅሁት ለማረጋገጥ፡፡

“እኔ የምሰጥህ አንድ ኪሎ ብቻ ነው፡፡ ሌላውን ከሌላ ሱቅ ዞረህ ልቀም፡፡” አለኝ

“ለምን?” “የተሰጠን ትዕዛዝ ነው፡፡ እኛ የለም ማለት ስለማንችል ብቻ ነው፡፡ ከአንድ ኪሎ በላይ ግን አልሸጥልህም፡፡” አለኝ ኮስተር ብሎ፡፡

“ማነው የከለከለው አልኩት?”

ኮስተር እንዳለ፣”ቀበሌዎች ከልክለዋል፡፡ ለማዳረስ አንድ አንድ ኪሎ ብቻ ነው የምንሸጠው፡፡” አለኝ የተለጠፈውን የስልክ ቁጥር እያሳየሁት “የለም ማለት እንጂ፤ ሁሉም ሰው በሚፈልገው መጠን መግዛት እንደሚችል ክልከላ እንደሌለው ነገርኩት፡፡ ደውዬ እንዳረጋገጥኩ ነገርኩት፡፡”

“ማነው ያለው አለኝ?” ደግሜ ስልኩን እየጠቆምኩ “ቀበሌዎች” አልኩት፡፡

“እኔ በስልክ አላመንም አለኝ፡፡” ታዲያ ይህን ሰው ደውዬ ባገናኘው፣ ሁለቱን ከማነታረክ ውጭ ምንም ፋይዳ አይኖረውም ብዬ ለስልኬም ሳንቲም ሳስቼ፤ እኔ መረጃውን እንጂ የነሱን ንትርክ ምን ሊረባኝ ብዬ ተውኩት፡፡ የቁጥጥር ስርዓቱን ለዘረጋችሁ ጥቆማዬን በድጋሚ በዚህ በኩል እነሆ፡፡

ስኳር ጥርዥ ብርዥ፡፡ ስኳር ወጣ ገባ፤ ከገበያ ፡፡ ይመጣል እንቃመሳለን ያልቃል፡፡ ደግመን እስኪመጣ ጠብቀን እንቃመሳለን ፡፡ ሩህ ሩህ ነጋዴዎች በእኩል በእኩል እንደ አመጣጣችን እና እንደ ድርሻችን እያፈሱ አንድ አንድ ኪሎ ይሰጡናል፡፡ ይህን ያህል ከላስን እኛም ይበቃናል፡፡

በሁለት ሃገራት ያሉ የሚመስሉ የመገናኛ ብዙሃን− የግል እና መንግስት ጋዜጠኝነት ሲፈትሽ

እስቲ ጥቂት ስለ ጋዜጠኝነት አላባውያን እናውጋ እና ከዚያ ወደ ተነሳሁበት ሃሳብ አንድ  ሁለት እያልን አብረን እንዘልቃለን፡፡ ከጋዜጠኝነት አላባዎች ቀዳሚዎቹ እና ዋነኞቹ ነፃ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃን ለህዝብ ማድረስ ናቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ለህዝብ ታማኝ በመሆን ለእውነት ዘብ መቆም ከአንድ ጋዜጠኛ ከሚጠበቁበት መሰረታዊ ግዴታዎች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ለእውነት ዘብ መቆም እና ለህዝበ ታማኝ መሆን፡፡ እነዚህ ሁለት ነጥቦች በዋነኛነት ላተኩር የፈልግኩባቸው ነጥቦቼ እንጂ ሌሎቹን ዘንግቼ አይደለም፡፡ ለእውነት ዘብ መቆምን እና ለህዝብ መታመንን ይዘን አብረን እንዘልቃለን፡፡ እነዚህን ሁለት ነገሮችን በዋነኛነት ያልቋጠረ ጋዜጠኛ ለሌሎቹ ግድ ላይኖረው ይችላል፡፡ ሁለቱን በመሰረታዊነቱ ከያዝን በኋላ ግን ልማትን ጨምረን በሃገራችን ያለውን የጋዜጠኝነት ትግበራ እንፈትሸዋለን፡፡ ልማት ስንጨምርበት ደግሞ ለአንድ ማህበረሰብ የጋዜጠኝነት እና የጋዜጠኛው ሃላፊነት እና አስፈላጊነት በጣም ከፍ ይላል፡፡ ሃላፊነትን የሚሸከም ደንደን ያለ ትከሻ እና ብርቱ ጉልበት ይልጋል፡፡ ጋዜጠኝነት ከባድ ሃላፊነት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ልማታዊ ጋዜጠኝነት፡፡

ከዚህ እንጀምር፣ ባሳለፈነው የመጋቢት ወር ሁለት የመጨረሻ ሳምንታት በሃገራችን ውስጥ የነበሩ አበይት የነበሩትን እና በግል እና በመንግስት የህትመት ውጤቶቻችን የዘገባ ሽፋን ያገኙትን ክስተቶችን እንቃኝ፡፡

በመንግስትም ሆነ በግሉ የህትመት ሚዲያ የዘገባ ሽፋን ያገኙ ዋነኛ ክስተቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አቀማመጠቸውም በዘፈቀደ ነው፡፡ በርዕሰ ጉዳያችን ላይ ተፅእኖ ስለማያሳድር ቅደም ተከተላቸውን አልጠበቁም፡፡ ዋነኛ ትኩረቴ ክስተቶቹ ናቸው፡፡ ዋነኛ ክስተቶቹም ፡-

  • የታላቁ የህዳሴ ግድብ አንደኛ አመት በዓል፣
  • ሃገራችን ከሌሎች የውጭ ሃገራት ጋር ያደረገቻቸው ግንኙነቶች፣
  • ከደቡብ ክልል ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ ተደረጉ የአማራ ተወላጆች
  • የመምህራን የእርከን ማሻሻያ የደሞዝ ጭማሪ
  • ጭማሪውን ተከትሎ የመምህራኑ ቅሬታ እና ተቃውሞ
  • በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች የተከናወኑ ልማት ተግባራት
  • የመድረክ ፓርቲ ስብሰባ ለማከናውን ማቀዱ እና ለስብሰባ የተከራየውን አዳራሽ በአከራዮቹ ስለመከልከሉ
  • የኢዴፓ ሊቀመንበር ቃለ መጠይቅ እና በገዢው ፓርቲ ላይ ያሰሙት ቅሬታ
  • ተቃዋሚዎች በህደሴው ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት ዋነኞቹ ነበሩ፡፡

እንግዲህ ልብ እንበል፣ ከእነዚህ ዋነኛ ክስተቶች በመንግሰት ጋዜጦች እና በግሉ ሽፋን ያገኙትን እንመልክት፡፡ ከሞላ ጎደል በግል ጋዜጦች ተመሳሳይ ዘገባዎች ሽፋን አግኝተዋል፡፡

 

በግል ጋዜጦች ላይ የወጡ ዘገባዎች፡-

  • የመመህራን የእርከን ደሞዝ ማሻሻያ
  • ጭማሪውን ተከትሎ መምህራኑ ቅሬታ እና ተቃውሞ
  • ከደቡብ ክልል ስለተፈናቀሉት አማራ ተወላጆች እና ስለደረሰባቸው እንደግልት
  • የመድረክ ፓርቲ ስብሰባ ለማከናውን ማቀዱ እና ለስብሰባ የተከራየውን አዳራሽ በአከራዮቹ ስለመከልከሉ
  • የኢዴፓ ሊቀመንበር ቃለ መጠይቅ እና በገዢው ፓርቲ ላይ ያሰሙት የስልጣን ወዳድነት  ቅሬታ
  • የታላቁ ህዳሴ ግድብ አንደኛ አመት በአል
  • ተቃዋሚዎች በህደሴው ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት

በመንግስት ጋዜጦች ላይ የውጡት፡-

  • የታላቁ የህዳሴ ግድብ አንደኛ አመት በአል አከባበር፣
  • የመምህራን የደሞዝ እርከን ማሻሻያ
  • የሃገራችን የውች ግንኙነቶች
  • በተለያዩ ክልሎች የተከናወኑ የተለያዩ የተፋሰስ፣ የማህበረሰብ እና ሌሎች ልማቶች በጣም በሰፊው፣ በጣም በዝርዝር

እነዚህ በሰፊው በፊት ገፅ ላይ ሽፈን ያገኙ የልማት ዘገባዎች ናቸው፡፡(ሁሉም ዘገባዎች ከየጋዜጦች የፊት ገፅ የተወሰዱ ናቸው፡፡)

ጋዜጠኝነት ለህዝብ አገልጋይነት እሰከሆነ ድረስ ሁሉም ክስተቶች በሁሉም ጋዜጦች ላይ በአግባቡ ሚዛናዊ ሆነው መዘገብ ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን መስመር አስምረው፣ ከዚህ መልስ ያንተ ከዚህ መልስ የእኔ፤ የግዛት አላስደፍር ባይነት ትግል ውስጥ የገቡ ይመስል፤ በግሉ እና በመንግስት ጋዜጦች የምናነበው የዘገባ ሽፋን፤ በጣም እጅግ ውስን በሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር በተለያዩ ሀገራት ያሉ እስኪመስል ድረስ በጣም የተለያዩ ዘገባዎችን ነው፡፡ ለዚህም መነሻው እንደ እኔ ግምት የግል ጋዜጦች የዋች ዶግ (የዘብ ሚና ጋዜጠኝነት ብዬዋለሁ) መርህን መሰረት አድርገው ስለሚሰሩ እና የመንግስት ጋዜጦች ደግሞ የመንግስት ፖሊሲ እና የትኩረት አቅጣጫን መሰረት አድርገው ስለሚሰሩ ልማታዊነት መርሃቸው ነው፡፡ የመንግስት ጋዜጦች እና ጋዜጠኞች ልማታዊዎች፡፡ የግሉ ደግሞ ዘቦች ናቸው፡፡ በመደጋገፍ ብትሰሩ . . .   አ. . . ቤ. . . ት. . .!!!                       ጋዜጠኝነት በምሉዕነቱ  ኢትዮጵያ ውስጥ ይከሰት ነበር፡፡

በሁለቱም መርህ ለሚሰሩት ጋዜጦች ግን ከላይ የተነሳሁባቸው ነጥቦች በሚገባ ይሰራሉ፡፡ ሙስናን፣ ብልሹ አሰራርን፣ ስልጣንን በአግባቡ አለመጠቀም እና ሌሎች ለልማትም ሆነ ለማህበረሰብ ደህንነት ጠር የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መታገል ማጋለጥ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ በሁለቱም መርህ የሚሰሩት ጋዜጠኞች ግዴታ ነው፡፡

በተጨማሪም Check and balance of power (የሃይል ምጥጥኖሽ እና ቁጥጥር) ማረጋገጫው ከፍትህ አካላት ውጭ አንዱ ጋዜጠኛው ነው፡፡ ፍትህ ሲዛባ፣ ሲጓደል የኃይል ሚዛን መቆጣጠሪያው ጋዜጠኝነት እና ጋዜጠኛው ነው፡፡ በልማታዊውም ሆነ በዘብ ጋዜጠኝነት ይህ አይቀሬ ነው፡፡ የተከፋ፣ የተገፋ፣ ድምፁ የታፈነውን ድምፁ የሚሰማበት፣ ብሶቱ የሚወጣበት አንዱ መንገድ ከፍትህ አካላት በተጨማሪም ወደ ፍትህ መቅረቢያ ማቋረጫ መንገዱ ጋዜጠኝነት ነው፡፡

የመጨረሻውን መስመር ሃሳብ ይዘን ደግሞ እንቀጥል፡፡ የተከፋ፣ የተገፋ፣ ድምፁ የታፈነውን ድምፁ የሚሰማበት፣ ብሶቱ የሚወጣበት አንዱ መንገድ ጋዜጠኝነት ነው በሚለው ከተስማማን፡፡ ለናሙና የመረጥኳቸውን የዜና ሽፋኖች መሰረት አድርገን ለዚህ ፅሁፍ ያነሳሳኝን” ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ አለ ወይስ የለም?” ለሚለው ክርክር ብያኔውን በጋራ እናሳልፋለን፡፡ አንድ ነገር እንዳትዘነጉብኝ፣ የናሙና የዘገባ ውጤቶቼ በወርሃ መጋቢት ብቻ ላይ የተውሰኑ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥም  ለውይይታችን አንዱ በቂ ነው፡፡

  • የመመህራን ደሞዝ እርከን ማሻሻያን እና ተከትሎ የተቀሰቀሰውን የመምህራኑን ቅሬታ

እነዚህን የመረጥኩበት ምክንያት እነዚህ ዘገባዎች በግል ጋዜጦች በሰፊው ሲዘገቡ በመንግስት ጋዜጣ ያኙት ሽፋን ግን ብዙም አልበረም፡፡ ለምን? የመምህራን ደሞዝ እርከን ማሻሻያ ሲጨመር በመጀመሪያ የተገለፀው በመንግስት ጋዜጦች እና ሚዲያዎች ነበር፡፡ አመርቂ የስራ ተነሳሽነት ከፍ የሚያደርግ ተብሎ ልማት፣ ልማት የሚሸት ዘገባ ስለነበር፡፡ ሁዋላ ላይስ ቅሬታቸው ለምን ቸል ተባለ? ቅሬታቸው ከፍ ብሎም በአንድ አንድ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሰራ ማቆም አድማ ሲደረግም ዝም ተባሉ፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እርምጃን መንግስት መውሰድ አስፈላጊ ነበር እና መግለጫ ሰጠበት፡፡ “ድብቅ አጀንዳ ያላቸው፣ የፀረ ሰላም ህገ ወጦች መምህሩን ተጠቅመው ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የታሰበ እንቅስቃሴ ነው እና ለዚህ አይነቱ ተቃውሞ መንገዱ ዝግ ነው ወደ ስራችሁ ተመልሳችሁ ጥያቄያቸሁን በአግባቡ አቅርቡ፡፡” ኮስተር ያለ አቋሙን መንግሰት ገለፀ፡፡ የመንግስት ጋዜጦችና ሚዲያዎችም አስተጋቡት፡፡ ይሄ ነገር ግን እሳት ባልነደደበት ጭስ . . . አይነት ነገር አይመስልም? ስለስራ ማቆማቸው እና ቅሬታቸው ተገቢውን ሽፋን ያልሰጡት የመንግስት ሚዲያዎች የመንግስት ማስጠንቀቂያ በምን ምክንያት ብለው ሊዘግቡ ደፈሩ፡፡ የሚዛናዊ እና አግባብ ያለው መረጃ ለህዝብ ማድረስ የሚለው የጋዜጠኝነት መርህ መተላለፍ አይሆንም?

ይብዛም ይነስም፣ በምንም መልኩ ቅርፅ እንዲይዝ ቢደረግም ተመጣጣኝ የሁለቱም ወገን ድምፅ  የተደመጠበት ዘገባን በአግባቡ በግል ጋዜጦች ለመስራት ተሞክሯል፡፡ አደራ አንድ ነገር እዚህ ጋር እኔ ለግል ጋዜጦች ጥብቅና እየተከራከርኩ አይደለም፡፡ የዚህ ፅሁፍ መነሻዬ “ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ አለ ወይስ የለም?” የሚለው የመከራከሪያ ሃሳብ ነው፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ደግሞ በግልፅ ተደንግጎ እየተሰራበት ያለው በመንግስት ሚዲያው ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የክርክር ሃሳቤን ማቅረብ የፈለግሁት፡፡ ልማታዊነት እኮ ለመንግሰት መወገን ወይም ለመንግስት የህዝብ ግንኙነት ሆኖ ማገልገል አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ራሱን የቻለ የመንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አለ፡፡ በልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ የመንግሰት ተሳትፎ (involvement) በተወሰነ ደረጃ አስፈላጊ እንደሆነ የዘርፉን ምሁራን ያሰማማል፡፡ ይህ ተሳትፎ ግን መጠኑ ከፍ ካለ ወደ ጣልቃ ገብነት አድጎ በሚዲያ አጠቃቀሙ ላይ መሰረታዊ ችግርን ይፈጥርና ፍትሃዊ ያልሆነ ስርአት ሊያሰፍን እንደሚችልም ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም፣ በልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚዲያው ዋነኛ ተግዳሮቶች አንዱ ሚዲያው በህዝብ አመኔታን ማጣትን ስለሚሆን፤ የመንግሰት ተሳትፎ መሆን ያለበት ሚዲያዎች ከሶሰቱ ነጥቦች አንፃር ተግባራቸውን መወጣታቸውን መቆጣጠር ነው፡፡

  • ትክክለኛ መረጃ ሰጪነታቸውን
  • አስተማሪነታቸውን እና
  • በልማቱ ስራ ህብረተሰቡን አሳታፊ ማድረጋቸውን ነው

ልማታዊ ጋዜጠኝነት ልማትን ማፋጠን እና ማገዝ ህብረትሰቡን ልማት ማነሳሳት ማስተማር እንጂ፤ በልማታዊነት ከለላ ድምፆችን ፀጥ ማድረግ አይደለም፡፡ በልማት አደናቃፊነት ፈርጆ መዝለል ተገቢም አይደለም፡፡ መንግስት በግልፅ የልማት አቅጣጫውን ተልሞ፣ ሚዲያው የልማት ስራውን እንዲደግፍ መመሪያዎችን አውጦቶ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከሌሎች በማደግ ላይ ካሉ ሃገሮች ተሞክሮ በመኮረጅ በሃገራችን ተግባርዊ እንደተደረገ እርግጥ ነው፡፡ ባግባቡ ልንተገብረው እና ልንጠቀምበት ግድ ነው፡፡ ለምን በአግባቡ አልተተገበረም? ተጨማሪ ምርመር ይፈልጋል፡፡ ከላይ በተነሳሁባቸው የመከራከሪያ ነጥቦቼ ወደ ብያኔ ብሄድ፣ አይደለም ልማታዊ ጋዜጠኝነቱ ዋነኛው የጋዜጠኝነት አተገባበርም በአግባቡ መፈተሸያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አይመስላችሁም?

ዥው ዥው የሚልን ቅርንጫፍ ተመልክቶ፣ ምስጥ ስለቦረቦረው ዛፍ ግንድ የአቋም ጥንካሬ እና ስለ ዛፉ ህልውና ማውራት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ከስንት አንዴ የሚነሳን አውሎ ንፋስ እንደሚያነሳው አቧራ ከስንት አንድ በሚነሱ ፕሮግራሞች ላይ መሰረት አድርጎ መደምደሙም . . .ችኩልነት ነው፡፡ ረጋ ብለን ብንወያይበት እኮ ልማቱንም ሆነ ልማታዊ ጋዜጠኝነቱ ሁላችንም በጣም የምንፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

እኔ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ውስጤ የቃጨለብኝ ላጋራችሁ እና እንሰነባበት፡፡ ቻው ልበላችሁ እና ስሜቴን ተጋሩኝ፡፡

የመንግስት፣ የመንግሰት እያልኩ ነው ከላይ የወረድኩት፡፡ መንግስት ይህን ጋዜጣ የቋቋመው ለእኛው ሃሳብ ማንሸራሸሪያ ከእኛው በግብር ከሰበሰበው ገንዘብ ነው፡፡ በጀቱም ምኑም የእኛው ገንዘብ ነው፡፡ እኔም እንደ ግብር ከፋይነቴ እነዚህ ጋዜጦች ላይ ድርሻ አለኝ፡፡ ግን የእኔነት ስሜት ሳይሰማኝ  ባእድነት እየተሰማኝ ነው ፅፌ የጨረስከት፡፡ መቼ ይሆን የእኔነት የሚሰማኝ?

የግል ጋዜጦችማ ያው የግል ናቸው፡፡ መረጃን ለእኛ፣ እኛን ደግሞ ለማስታወቂያቸው ሸጠው ህልውናቸውን የመሰረቱ፡፡ ስለመረጃ አቅረቦታችሁ ግን ምስጋናዬን በስውር፡፡ ከመሃመድ ሰልማን አንድ ሃሳብ ተበድሬ ልመርቅለችሁ- ኢቲቪዮጵያን፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ተተግብሯል ለምትሉኝ በሙሉ ምናልባት ይህን ጉዳይ በኢቲቪዮጵያ እንፈልገው ይሆን?

 

በአዲስ አድማስ ጋዜጣ መጋቢት 20፣ 2004 የታተመ

ኢትዮጵያዊ መፈክሮች (Mottoዎች)

በዘመን ደግም ይሁን ክፉ፤ብዙ ይሰማል ባዙ ይታያል፡፡ ብዙ ብዙም ይታለፋል ብዙም ነገር ይለወጣል- ወይ አሻራው አለያም ጠባሳው ይቀራል፡፡ ባርያ ፍንጋላ፣ ጭሰኛ መሳፍንት ነገስታት በየዘመናቸው የራሳቸውን ፣መፈክር እያሰሙ ግባቸው እያስቆጠሩ አልፈዋል፡፡ በባርነቱ ዘመን “ለገዢዎቻችሁ ተገዙ” መሰለኝ የወቅቱ መፈክር(Motto)፣ በጭሰኛው የንጉሱም ዘመን”የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን” ነበር የወቅቱ መፈክር(Motto)፣ “የሚወደንና የምንወደው ህዝባችን” እያሉ መሪዎቻችን “የሚወዱትንና ሚወዳቸውን” ህዝባቸውን በፍቅራቸው አስረው፤ በድንብ እና ስርዓታቸው ሸንግለው በግፍ አኑረውታል፡፡ የግፍ ፅዋው ሲሞላ ታዲያ. . . ተራማጆች በቀሰቀሱት አቢዮት “አንድነት ሃይል ነው”አሉና ተማሪው፣ ሰራተኛው፣ ወታደሩ… ህብረተሰቡ በሙሉ፤ በንቅናቄ

“አቆርቋዥይውደም

ያለ ምንም ደም

ኢትየጵያ ትቅደም”ን ዘምረው

ህብረተሰባዊት ኢትዮጵያን መሰርተው አንድ ቋንቋ ተናግረው፣ አንድ ጥይት ተኩሰው፣ አንድ አቢዮት አፈንድተው፣ አንድ ትውልድ ፈጅተው፤ በጡጫ እና በግልምጫ ልቀው ከወጡት የወቅቱ መሪ ስም ጋር. . .ወደፊት፣ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” እያሉ ይፎክሩ ነበር፡፡ በየመድረኩ በሚደረጉ ህዝባዊ ስበሰባዎችና ንግግሮች ላይም “እናት ሃገር ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ፣”ህብረሰባዊነት ይለምልም”፣ “. . . ለኢምፔሪያሊስቶች “

በዚያው ዘመን ታዲያ፣ የጦርነቱ ጫና አይሎ የወቅቱ ወጣት ለወታደርነት ሲታፈስ በፍርሃት ይሁን በወኔ “ይሰጠን ይሰጠን ቺቺ . . .መቺ”(የጎደለውን ሞልታችሁ አንብቡ፤ ቃሉን በአሁኑ ሰዓት መጠቀም የሚያስከፋቸው አይጠፉም እና ትቼዋለሁ)”ይሰጠን ይሰጠን ክላሽ ሰላሳ ጎራሽ” በማለት ዘምረው  ፎከክረው ሃሩር እና አረር በልቷቸው የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ምስጋና፣ ለዘመኑ መሪዎቻችን ጦርነትን በእኛ ይብቃ ላሉት ይሁንና፤ አሁን ጦርነት ስለሌለ የዚህ ዘመን ወጣቶች ውትድርና ጦርነት እና አፈሳ የለብንም፡፡ ዘመቻ ግን አለብን፡፡ ለሁሉም ነገር ዘመቻ፡፡ በዚያው ወቅት እናቶች በየቀበሌው ተሰብስበው ልጆቻቸውን ለጦርነት ልከው፣ ስንቅ እያዘገጁ የላይኞቹን መፈክሮች እና “አቢዮቱ አይቀለበስም”፣ “ሞት ለ . . . ” (በተመሳሳይ የጎደለውን ሙሉልኝ) ተጨማሪ መፈክራቸው ነበር፡፡ አሉ፡፡ የእስካሁኑ የሰማሁት ነው የፃፍኩላቸሁ፡፡

ግራ ዘመሞች ትግላቸውን ከሰፊው ህዝብ ጋር አሳልጠው ከገጠር ወደ ከተማ መሩትና ድላቸውን “ብሶት የወለደው ጀግናው . . . ለሰፊው ህዝብ . . . ተቆጣጥሮታል” አሉ እና ስልጣኑን ግን . . . (ሃያ ዓመት አለፋቸውም አይደል? ይህን በሹክሹክታ ስሙልኝ) እራሳቸው ያዙት፣ አሉ፡፡ይህም የሰማሁት ነው፡፡

አዲስ ትክክለኛ ዘመቻ በአዲስ የትኩረት አቅጣጫ የጋራ ጠላታችን ድህነት ላይ ጦርነት ታወጀበት፡፡ ድህነት . . .

ያኔ፣ መሪዎቻችን እስኪ ከወደፊት ለሃገራችሁ ካሏችሁ ራዕዮች ውስጥ ጥቂቶን ሲባሉ?የአመቱን ቁጥር የተናገሩት መቼም አየዘነጉት፤ በዚህ ዓመት ውስጥ ህዝባችን በምግብ እህል ራሱን ይችላል በቀን ሶስቴ ይመገባል፡፡ ከዚህ ዓመት በኋላ ደግሞ ቅያሪ ልብሶች. . . በፈገግታ ደምቀው ተናግረው ነበር፡፡ ምን ያህሉ ተሳክቶላቸው ይሆን?

“ታግለን ወድቀን ከግፍ አገዛዝ ነፃ አደረግናችሁ” አሉን፡፡  አሁን ደግሞ በልማት ጎዳና… አዲዮስ ድህነት አስፎከሩን፡፡ በእኩልነትን አስጨፈሩን፡፡ ህብረ ብሔርነትን አስዘመሩን፡፡ ከመፈቃቀር፣ከመዋደድ እና ከመዋለድ በላይ መቻቻልን አስፎከሩን፡፡

ዘመን ዘለልን . . . ዘመንን ቆጠርን :: ሽብረተኝነት ይውደም(ይቅርታ ይውደም የሚለው ቃል የቀድሞው ስርዓት አገላለፅ ነው) ይውደም የሚለው እንዋጋለን በሚለው ተተክቶ ከይቅርታ ጋር ይነበብ፣ ጠባብነት ትምክህተኝነትን እንዋጋ፡፡ ቀንደኛ ጠላታችን ግን ድህነት እንዋጋለን፡፡ አንድ ሰሞን ፎክረናል፡፡

አሁንም ዘመንን ዘለልን በድህነት ላይ እንደፎከርን ምዕተ ዓመቱ መጣ፡፡ ኮሜዲያን ክበበው በአንዱ የቀልድ ሰራው ውስጥ፣”ከብድር ሳንወጣ ደሞ ልንበደር ሚሊኒም መጣ” እንዳለው በሚሊኒየሙ ሚሊኒየም ጠጅ ቤት፣  ሚሊኒየም ቁርጥ፣ ሚሊኒየም ኬክ ቤት፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም፣ ሚሊኒየም ምን ይሁን ምን ሳይገባን፤ የሚሊኒየም ክብረ በዓል ፊት የኮንደሚኒየም ቤት እጣ ካልተሳካላቸው ውስጥም “እኔ እንግዲህ ኮንደሚኒየሙ አልሆነልኝም እስቲ ምሊኒየሙን ደግም እሞክራለሁ፡፡” ብላዋል አሉ፡፡ እስራ ምዕት ብለን ቦታና ስሙን ቀይረን ፎከርንበት፡፡ በሚሊኒየሙ ላይም ዘመትንበት፡፡

ልማታዊነት ሌላኛው መፈክር፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ልማታዊ ምሁር፣ ልማታዊ ባለሃብት፣ የልማት አርበኛ በሰፊው ተፈጠሩ ለቀጣይ የሃገሪቱ የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል (ቋንቋውን አሰካካሁት)፡፡ ወጣቱ፣ ገበሬው፣ ምሁሩ፣ ባለሀብቱ በልማታዊነታቸው ተሸለሙ፡፡ ከወጣቶቹ ውስጥ ግን እኔ አልተሸለምኩም፤ ምክንያቱም መንግስት በፈጠረው ምቹ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቼ ወጣቱን በማስተባበር እና በማደራጀት መንግስት በተለመው ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ እና ስትራቴጂ ውስጥ በጉልህ እንዲሳተፉ በማድረግ እረገድ የተሰጠኝን ሃላፊነት ያለኝ አቅም ሁሉ አሟጥጬ በመጠቀም ረገድ በሰፊው ተሳትፊ ስላልነበርኩ መሰለኝ፡፡ እንጂ እኔም እኮ ግን ልማታዊ ወጣት ነኝ፤ ስራዬን በአግባቡ እየሰራሁ ነው፡፡ እኔ እደንደገባኝልማታዊነት ስራን በአግባቡ መስራት ነው፡፡ (ግን ቀበሌ ለጉዳዬ ካልሆነ በስተቀር ማቶስስ አልወድም፡፡)

ከኔ ለየት ያላለ የአንድ ገበሬን ሃሳብ ለካፍላችሁ እና ወደ ጉዳዬ ልሂድ፡፡ የራሳቸው ራዲዮ በየአስራ አምስት ቀኑ፣ ይህን የልማት ጀግና አርበኛ የሜዳይ ሽልማት ታስደምጣቸዋለች፡፡ አንዱ የልማት አርበኛ ከዚህን ይህል ሄክታር ይህን ያህል ኩንታል ባለፈው ዓመት አግብቻለሁ፤ በዚህ የምርት ዘመን ደግሞ በእጥፍ እንደማመርት . . (ቁጥሩ ስለሚያስደነግጥ ይቅርብን) መንግስት  የፈጠረው ትክክለኛ እና ምቹ የልማት. . . (አልጨርሰውም፤ ምክንይቱም አትጨርሰው ይቅር ሰልችቶናል ትሉኛላችሁ ወይም ደግም ኢሬቴድን አዲስ ዘመንን ጨምሮ እንደ ሚዲያዳሰሳው ልዳስሰው አልፈልግም፡፡ የምፈራው ግን የእንጀራ ገመዴ ጎትቶ እዚያ እንዳይከተኝ ነው፤እኔም “ልማታዊ”ጋዜጠኛ…እንዳትስቁብኝ አደራ፤ፀልዩልኝ፡፡) በጅምር የተውነውን የልማት አርበኛ ንግግርም አብራ ታስደምጣቸዋለች፡፡  እናም ገበሬው የልማት አረበኛውን ጥሩ ጥሩ ተሞከሮዎች ማሳቸው ላይ ሞክረው የተባለው ምርት አልገኝ ሲል፤ አይ በቃ ወይ እኔ ልማታዊ ግብርናን በአግባቡ እና በትክክለኛው መንገድ አላከናወንኩም ወይ ደግሞ፣ በእኛ ቀዬ መንግሰት የቀየሰው ትክክለኛ እና ምቹ የልማት . . . .ገና አልደረሰም፡፡ ብለዋል፡፡ አሉ፡፡

አሁንም ዘመን ተሻገርን የአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ፡፡ እሱን ተከትሎ ብዙ የተባለለት የአባይ ግድብ (አሜን፤ ለግድቡ) አንድ በፌስ ቡክ ላይ ያየሁት “ከቢዮንሴ ናይት” ክለብ ቀጥሎ “አባይ ግድቡ ጠጅ ቤትን” ነው፡፡ ከህዳሴው ግድብ  በፈትም ሆነ በኋላ የሰለቸኝ፣ ለጆሮዬ አኞ የሆነው መፈክር ግን የአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ነው፡፡ ከላይ አስከ ታች የመንግሰት ሹማምንት በሙሉ ይህን ቃል የረሳ . . . ብለው  የተማማሉት ምን ነገር እንዳላቸው እንጃ (በዚህ ሁኔታ በየቤታችው ከየቤተሰባቸው ጋር ላለማለታቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡) “ታላላቅ” ሹማምንቱ “ታላላቅ” የልማት ፕሮጀክታቸውን፤ “ንዑሳን” ባለስልጣናቱም እንደ ስልጣናቸው አነስ ያሉትን  ሲመርቁ ወይ ደግሞ የመሰረት ድንጋይ ሲያስቀምጡ ከሚሉት መሃል “…ይህ ፕሮጀክት መንግሰት በአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ውስጥ ካስቀመጣቸው ዋነኛ አጀንዳዎች…”የመግቢያ አረፍተ ነገራቸው ነው፡፡ ከልማታዊ አንቀሳቃሾቻችን እና ተንቀሳቃሾቻ በተጨማሪም በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ስፖርተኞቻችን እና የስፖርት ጋዜጠኞቻችንም “…ይህ ስፖርታዊ ውድድር መንግሰት በአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ውስጥ ካስቀመጣቸው…” ማለታቸው ተለመደ፡፡ የሚገርመኝ ነገር ይህ መንግስት የሚባለው ምንድነው? ማነው? ባለስልጣኖቻችን “መንግሰት” የሚሉት ሲከሱም፣ ሲወቅሱም፣ ሲመርቁም ሆነ ሲራገሙ “…መንግስት…” እያሉ የሚሸሸጉበት መከለያቸው፤ አቋራጭ ማምለጫቸው፤ የነሱ ስብስብ መሆኑን ረስተውት ነው? ወይስ ሌላ ከእነሱም ከእኛም እውቅና ውጪ የሆነ …አለ እንዴ?

ይህም መንግስት እኔን በቀጣይ በአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ በልማታዊ ወጣትነት እንደሚሸልመኝ ተስፋ አለኝ፡፡ ሁሉም ነገር ለአምስት አመቱ የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ይሁንና፡፡ አንድ ስጋት ግን አለኝ፤ የመንግሰትን ሌቦች ግቤን እንዳያደንቅፉት፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህን የመንግሰት ሌቦችንም ቢሆን መንግስት በእንጭጭነታቸው ከምንጫቸው የሚያደርቅ የመፍትሄ ሃሳብ አስጠንቶ ጨርሶ በቅርቡ ተግባራዊ ስለሚያደረግ ስጋቴ፣ ከስጋት በዘለለ ምንም እንከን እንደማይገጥመው ተስፋ አለኝ፡፡

ከእዚሁ ከአምስቱ አመት የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን እቅድ ውስጥ ሳንወጣ፤ የእቅዱን ይፋ መሆን ተከትሎ በየቦታው የተሰቀሉት የ”እነሱ እስኪደርሱ እኛን ተመልከቱ” ፎቶግራፎች የተገባውን የተስፋ ቃሉን ሳይጠብቁ፣ የታቀዱትም ሳይደርሱ እነሱ እራሳቸው ቀድመው በተፈራራቂ የአየር ለውጥ ከመወባቸውም ባሻገር በንፋስ ጎብጠው ተስፋችንን ይዘው በመጥፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ የምንኖረው በተስፋ ነው፡፡ ይህ የይሆንልናል ተስፋም እንዳይጠፋ እነዚህን ፖስተሮች የተከላችሁም ያስተከላችሁም ሁላችሁም በተስፋ ስንጠብቅ፣ በተስፋ ስንኖር . . . አደራ እንዳትረሷቸው፡፡ ፎቶዎቻቸው ጥለዋቸው የጠፉ ፕሮጀክቶችን አንዱን እንኳ ከመሬት ሳናይ፤ የአፍፃፀም ችግር የአቅም ምናምን ሰበባሰበቦች ሌላ ስንት አመት ያስጠብቁን ይሆን?

ሁሉም ነገር ወደ ትራንስፎርሜሽን እና እቅዱ!!! ከመንግስት ጋር . . .

  • በአዲስ አድማስ ጋዜጣ መጋቢት 28፣ 2004  የታተመ

ኑዛዜ

በስተ መጨረሻ ሲሆን ፍፃሜዬ

አይቀሬ ነውና ወደአንተ መንገዴ

በፍጥረት ህግጋት በአርምሞ ተይዤ

በሰብም ስርዓት በከፈኔ ተጠቅልዬ

በመግነዝም ተገንዤ ፡፡

እናም . . . እለምንሃለው

አምላኬ . . . ጉዞዬ .  . .

ከካህናቱ ዝማሜ

ከመላእክትህ ምስጋና

ከአእወፋት ቅላፄ

ከህግ ዑደትህ

ቅኝትን ፈጥሬ

ገምጄ አዋህጄ

በስጋም በነፍሴ

በተመስጦ ተጠምጄ

በምስጋናህ ቅኔ ተመስጣ ነፍሴ

ከህይወት ምድጃ ልውረድ ተገፍቼ ፡፡

መቼም . . .

በማላውቀው . . .  በማልፈታው ቀመር

ህላዌ ተሰጥቶኝ ከምድር ስፈጠር

ሁሌም  አንድ ነገር ብቻ አንድ ነገር

ህይወት  ለማሸነፍ

ስታትር ስታትር

ስንፈራገጥ ስጥር

ታዲያ በስተመጨረሻ

አይቀሬ ነውና

ወደ አንተ ጉዞዬ

እንዲህ ይሁንልኝ. . .

እልም ልበል ስልም

በዝማሬው መሃል

በቅኔው ዘረፋ

ከቁመቱ መሃል

ስልም  ትበል ሹልክ

ትነጠቀው ነፍሴ

በአርምሞው መሃል

ስታቀርብ ውዳሴ

በስተ መጨረሻ ሲሆን ፍፃሜዬ

አይቀሬ ነውና ወደአንተ መንገዴ

በፍጥረት ህግጋት በአርምሞ ተይዤ

በሰብም ስርዓት በከፈኔ ተጠቅልዬ

በመግነዝም ተገንዤ ፡፡

እናም . . . እለምንሃለው

አምላኬ . . . ጉዞዬ .  . .

ከካህናቱ ዝማሜ

ከመላእክትህ ምስጋና

ከአእወፋት ቅላፄ

ከህግ ዑደትህ

ቅኝትን ፈጥሬ

ገምጄ አዋህጄ

በስጋም በነፍሴ

በተመስጦ ተጠምጄ

በምስጋናህ ቅኔ ተመስጣ ነፍሴ

ከህይወት ምድጃ ልውረድ ተገፍቼ ፡፡

መቼም . . .

በማላውቀው . . .  በማልፈታው ቀመር

ህላዌ ተሰጥቶኝ ከምድር ስፈጠር

ሁሌም  አንድ ነገር ብቻ አንድ ነገር

ህይወት  ለማሸነፍ

ስታትር ስታትር

ስንፈራገጥ ስጥር

ታዲያ በስተመጨረሻ

አይቀሬ ነውና

ወደ አንተ ጉዞዬ

እንዲህ ይሁንልኝ. . .

እልም ልበል ስልም

በዝማሬው መሃል

በቅኔው ዘረፋ

ከቁመቱ መሃል

ስልም  ትበል ሹልክ

ትነጠቀው ነፍሴ

በአርምሞው መሃል

ስታቀርብ ውዳሴ

“ቢግ ዲስካውንት”. . . ወይስ “ሜኪንግ ቢግ አካውንት?”

የዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ከማጀት ጉድ ጉድ በደጅም በውጭም ወንዱም ሴቱም ተፍ ተፍ ጠደፍ ጠደፍ ደስ ሲል፡፡ ሩጫው በቃ ሁሉም በአቅሙ ሁሉም በኑሮ ደረጃው ይሮጣል፡፡ እንደ ኑሮው በዓልን ለማክበር፤ ለመዘከር፡፡
ባዛር በየቦትው ይዘጋጃል፡፡ ከቅርቤ ልጀምርና ያየኋቸውን ላስቃኛችሁ ስድሰት ኪሎ አራ ኪሎ በካዛንችስ በኢግዚቢሽን ማዕከል . . . ጎዳናዎች ይደምቃሉ ድንኳኖች ይተከላሉ፡፡ የሚሸጡ ከቤት ውስጥ ትላልቅ ቁሳቁሶች ሶፋ፣ አልጋ፣ ቁም ሳጥን ጀምሮ እሰከ ትንንሾቹ ሹካ እና ማንኪያ ድረስ፤ ለእይታ እና ሽያጭ ይሰላፋሉ፡፡ የቤት ማሳመሪያ አበቦች እና የተለያ ጋጣጌጦች፡፡ ልብስ ጫማ፣ የምግብ ሸቀጦች፣ እነማር ሸሮ በርበሬ ቅቤም ቦታቦታቸውን ይዘው ተሰድረዋል፡፡ ዞር ዞር ብሎ ድካም ለትሰማው አረፍ ከሚልበቸው መቀመጫዎች ጋር በዛሩ ድጋፍ ሸጭነት ምግብና መጠጥም በየቦታው አሉ፡፡ ቡና ሻይ ቀለል ካሉቱ ጀምሮ እሰከ ጠጅ ለውሃጥም እና ጨዋታ ማድመቂያ በባዛር ቦታዎች ተሰልፈዋል፡፡ ሞንታርቦዎች ተተክለው አድንቋሪ ሙዚቃዎች በጠዋት በቀን በምሽቱ ይለቀቃል፡፡ እየገበዩ መዝናናት፡፡
ያለው ቤቱን ውስጡን እንደ አዲስ ይሰራዋል ከማጀት እቃው ከእነሹካ ማንኪያ ጀምሮ እሰከ ሶፋ በአዲስ ይተካል፡፡ የመብራት ጌጦች፣ አበባዎች፣ ስዕሎች… ለበዓል ካለው ቤት የሚታደሙ ናቸው፡፡ በዓል ጥሩ ነው ሁሉን እኩል ያንቀሳቅሳል ያጣድፋል፡፡በተመሳሳይ ሃሳብ ያናውዛል፡፡ ያለው አምሮና ደምቆ በዓሉን ለመቀበል እቃውን ቀይሮ ቤቱን ሲያሰማምር፡፡ የሌለው ሀሳቡን መቀየሩ አይቀርም፡፡ መቀየር ከሚባል መቀመር ቢባል ይሻላል፡፡ ከዘወትር መደበኛ ሃሳቦች በተጨማሪም በአሉን እንደቤት እንደ አቅም እንዴት ይታለፋል በአእምሮ ውስጥ ለስሌት የሚሰለፉ ሃሳቦች ናቸው፡፡

ለልጆች ልብስ፣ ለወዳጅ፣ ለጓደኛ እንዲሁም ለፍቅረኛ የአመት በዓል ስጦታ ለመግዛት ገበያውን መጎበኘት አይቀርም፡፡ እንዲሁም ዞሮ ገበያ የመቃኘት ሱስ ላለበት ለእንደ እኔ አይነቱም የዓውዳመት ገበያ ግርግር ደስ ይላል፡፡ የዓመት በዓል አንዱ ውበቱ ይህው የገበያው ግርግር ነው፡፡ እናም በባዛር ዝግጅቶች መሃል ዓይኔ ያረፈበት እቃ እየጠየቅሁ ቁልቁል ወረድሁ፡፡ ከዛም ሱቆቹን ጎበኘኋቸው፡፡

ታላቅ ቅናሽን ካንጠለጠሉቱ ቡቲኮችም ሲገባ አስደናጋጭ ቁጥሮችን እንሰማለን፡፡ እነጃኬት ቀድሞ የሙክት መግዣን እነ ቲሸርት የአሁኑን የእነ ዶሮ ዋጋን ተጋርዋል፡፡ የቀድሞ የዶሮ ዋጋ አሁን ምናልባት ጥሩ ካልሲ ለመግዛት ትንሽ የኪስ ድጎማ ትፈልጋለች፡፡
በየቦታው ገበያ ደርቷል፡፡ ነጋዴዎቻችን የመጨረሻ የማጣሪያ ሽያጭ በሚመስል ሁኔታ፣ የበዓል ልዩ ቅናሽ፣ ቤሱቆቻቸው በረንዳ ላይ ከእንኳን አደረሳቸሁ ካለበት ባለቀለም ባነር ጋር ሰቅለዋል፡፡ ምን ያህል ሸጠው ምን ያህል እንደሚያተርፉ በማሰብ ልባቸው ደግሞ ከውስጣቸው ተሰቅሏል፡፡

“የወንድ ጫማ በአንድ መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ብር ብቻ”፡፡ ከጫማ ሱቁ የውጭ ግድግዳዎች የተለያዩ ቦታዎች ላይ አይን እንዲስብ ተደርጎ ተለጥፏል፡፡ ለእንደ እኔ አይነቱ ይህ ከሎተሪ እጣ አይተናነስም ኪሴ ውስጥያለኝን ብር እያሰላሁ ዘው፡፡ የእጣውን እፍታ ካናት ከሁሉ ቀድሜ ላነሳ፡፡ አይኔ ያረፈበትን ጫማ አንስቼ በስስት፣ በፍቅር እያየሁ ዙሪያዋን ገልበጥ ገልበጥ አድርጌ ከመለካቴ በፊት ስመለከታት ሦስት መቶ ሃምሳ የሚል ቁጥር ተለጥፎበታል፡፡ ትምህርት ቤትም ሂሳብ ላይ ሽግር ስለነበር፣ ግራ እየገባኝ ቁጥሩን የሚያስረዳኝን ሰው በአይኔ ሳፈላልግ፡፡ ሁሉም የሱቁ የሽያጭ ሰራተኞች ስራ በዝቶባቸዋል፡፡ ደንበኛን በማስተናገድ ተወጥረዋል፡፡ ወንድ የቀረ አይመስልም በአንድመቶ ሰላሳ ዘጠኝ ማግኔት ተሰብስቧል፡፡ ሴቶችም አሉ፡፡ እነሱ የመጡት ይመስለኛል ለእጮኞቻቸው ወይ ለባሎቻቸው አለያም ለፍቅረኞቻቸው የበዓል ስጦታ ለመግዛት መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ ምክንያቱም ቅናሹ የሚመለከተው ወንዶችን ብቻ ነው፡፡ አበክሬ ጉዳዩን የሚያስረዳኝ ሰው በአይኔ አፈላለግሁ፡፡ አይ ፈገግታ ተውኝ ልብን ይሰውራል፡፡ እየተፍለቀለች መጣችልኝ ፡፡
“ይህ ነገር ምንድ ነው?” ቁጥሩን እያሳየሁ ጠየቅኋት፡፡ ልጅት ቸር ናት ከፈገግታዋ ቅንጣት ሳትቀንስብኝ “የመሸጫ ዋጋው ነው አለችኝ፡፡” ግራ እየገባኝ “እንዴት ነው ነገሩ ታላቅ ቅናሽ የተባለለት፣ አንድመቶ ሰላዘጠኙስ የለም ወይስ አልቋል?” ጥያቄው ለእኔም ለእሷም ነበር፡፡ “እሱማ ያውልህ እዛ ጋር አለችኝ፡፡” ከወደ ጥግ አንድ መደርደሪያ እየጠቆመችኝ፡፡ ዋጋቸው እንጂ ጫማዎቹ አያምሩም፡፡ የልጅት ፈገግታ በቀላሉ የሚላቀቁት አይነት አይደልም፡፡ ልቤ ተሁለት ተከፈለ፡፡ ከኪሴ እና ክልጅት ፈገግታ፣ እና ሶስት መሆኑ ነው እንዴ? ከጫሚቲ፡፡ የቱን ልምረጥ? እንደ መጀነን፣ የወንድነትም ኩራት አለ አይደል? በሴት ፊት ጠይቄ ሳልገዛ መሄዱም ሊያሳፍረኝ ነው፡፡ ጫማይቱን አገላብጬ ካየኋት በኋላ የመጣው ይምጣ አልኩና ለካኋት፡፡ ታምራለች፡፡ ሰፋችኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ “ውይ አምራብሃለች አልችኝ፡፡” የልጅትን ፈገግታ እንዳትዘነጉብኝ፡፡ “ግን. . . ” አልኳት፡፡ እግሬን ዞር ዞር አድርጌ እያሳየኋት፡፡ “ሰፋህ፡፡” አለችኝ እና ወዳ ጓዳ ገባች ልኬን ፍለጋ፡፡ ልኬ እንዲጠፋ አጭር የልመና ፀሎት አደረስኩ፡፡ ልኬ ካልጠፋ እኔ በፕሮግራሜ መቃወስ የተነሳ መጥፋቴ ነው፡፡

ልጅት ፈገግታዋ ትንሽ አነስ ብሎ፤ ሌሎች ሁለት ጫማዎችን በእጇ ይዛልኝ መጣች፡፡ “እነዚህን ሞከራቸው፡፡ ይችኛዋ አልተገኘችም፡፡” አለችኝ መጀመሪያ የመረጥኳትን እያሳየችኝ፡፡ በልቤ የምሰጋና ፀሎት ችግሬ ለገባው አምላክ፡፡ ለልጅት ደግሞ የእሰከ አሁኑን የፈግታዋን ሁሉ አፀፋ በአንዴ አወራርጄ ፣”ው ይ እነዚህማ አይስቡም፡፡” አልኩና እራሴን ካስገባሁት ወጥመድ ሹልክ፡፡ አልኩላችሁ፡፡

በዚህ ይለፍልህ ያልተባልኩት እኔ ወጥቼ ደፋ ደፋ ስል በጃኬቱም፣ በኮፍያውም፣ በመስተዋቱም በሁለነገሯ ታላቅ የበዓል ልዩ ቅናሽ የተለጠፈባት ቡቲክ ደረስኩ፡፡ ገባሁ፡፡ አይኔ ያረፈበትን ጃኬት ጠየቅሁ ፡፡ እዚህ የሽያጭ ሰራተኘው ወንድ ነው፡፡ “ስድስት ከሃምሳ” አለኝ የቅናሽ ዋጋ የሚል አንብቤ ነው የገባሁት፡፡ “ከታላቁ የበዓል ቅናሽ በፈት የጃኬቱ ዋጋው ስንት ነበር?” ኮስተር እንደ ማለትም እየቃጣኝ ነው፤ ጠየቀኩት፡፡ ወንድ ነዋ፤ ብረት ለብረት፡፡ አንድ ሺ ለማለት ምን ይፍራ ወይ ምን አፉን እንደያዘው እንጃ “ዘጠኝ ከሰማንያ አለኝ፡፡” “ኧ ኧ ኧ ኧ” በውስጤ ነው፤ ከተወሰኑ አመታት ይህ ብር በፊት የቅልብ በሬ ዋጋ ነበር፡፡ አሁን ተደራድሬ ዋጋ ባፈርስበትም ምንም የሚይዘኝ ነገር የለም፡፡ በቀላሉ ጨዋታውን አበለሻሸሁበት፡፡ ነገር አስቀየስኩ፡፡ እንደማልገዛው በደንብ ሲገባው በነገር ገባልኝ፡፡ “ድሮም እኮ ወንዶች አትገዙም አለኝ፡፡” “እንዴት? ማለት?” ላለመረታት፡፡ “ወንዶች ብራችሁን ለሴቶች እንጂ . . . ሴቶቹ ናቸው ሚገዙት፡፡ አምረው ለመታየት ይገዛሉ፡፡ ካለበሱ መቼ ያምሯችኋል? ካለበሱ ካልዘነጡ አታይዋቸውም፡፡ እናንተ ለእነሱብራችሁን ስትጨርሱ፣ እነሱ ደግሞ ለልብስ ይጨርሱታል፡፡” አለኝ፡፡ ብዙ ነጥብ አስቆጠረብኝ፡፡ ብዙ ተቆጥሮብኝማ ዝም አልልም አልኩና፣ እንዴት ነው ይህ ጉዳይ አንተን አይመለከትም? አልኩት፡፡ “ወንድ አይደለሁ፤ የጋራ ችግራችን ነው፡፡” አለኝ፡፡ ይህችን አስምሩልኝ፡፡ አንድ እኩል፡፡
የበዓል ግርግር ተሟሙቋል በየቦታው፡፡ ከባዛሩም፣ ከዐውዳመት ገበያው ሻጭ እና ገዥ በዋነኛት ጎራው ለይተው ለግጥሚያ ተዘጋጅተዋል፡፡ ከሱቅ ዋጋ እንውጣ እና ሌሎቹን እንቃኝ፡፡
ከከብት ተራ ሰንጋ ከትንሽ ሺ ብሮች ጀምሮ እሰከ አርባ ሺ ብር ድረስ (አንደ ቅልብ በሬ ከአደስ አበባ ውጭ ከአንዲት ትንሽ የወረዳ ከተማ ለብሶ የተጫወተው ቁጥር ማለቱ ይቀለኛል፤ የተሸጠበት ዋጋ)፣ ዶሮ ከሰማንያ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ እና ሰባ የደረሱባቸው ገበያዎች ነበሩ፡፡ በግ እና ፍየል ከአንድ ሺ ብር ጀምሮ፤ የድልብ በግ እና ፍየል ዋጋ ደግሞ እሰከ ሰባት እና ስምንት ሺ ብር ድረስ ከሜዳ ገብትው በአመት በዓሉ ሸምጋይነት ይባል ዳኝነት ሻጭ እና ገዢ ተጋጥመውበታል፡፡ ማን እንዳሸነፈ ውጤቱ በሚስጥር እንደተጠበቀ ጀንበር ስትጠልቅ ተለያተዋል፡፡ ቅቤ አንድ መቶ ሰባን ለብሶ በመሃል ተጨዋችነት ጥሩ ሲንቀሰቀስ ለብዙዎች በአድናቆት ሲፈርም ውሏል፡፡ በበዓል ቅቤ ከሁላችንም ቤት አይጠፋም፣ የተለመደ ክስተት፡፡ የእነ ሽንኩርት፣ ቃሪያ እና መጥበሻ ዋጋ ማን በትንንሹ ይደክማል በሚል እሳቤ ሆን ተብሎ ተዘሏል፡፡ ዋጋቸው እንደ ጨመረ ግን ተሰምቷል፡፡

እናም እኔ የገረመኝ በዚህ የበዓል ገበያ ነጋዴዎች በጣሙን እየቀነሱልን ወይስ በጣሙን ከኑሮችን እየቀነሱብን? በዓመት በዓሉ፣” ቢግ ዲስካውንት” ወይስ “ሜኪንግ ቢግ አካውንት”፡፡ መልካም የበዓል ሰሞን፡፡

ያሰበውን የሆነ፣ የፈለገውንስ የኖረ፤ ማነው?

በህይወት ዑደት፣ በዘመን ስሌት ግዜ ሲሰፈር ፣ህያው ፍጥረት ሁሉ ያልፋል፡፡  ሕይወት የገባው፣ ታግሎ ያሸነፈው፣ አሻራውን በጉልህ አትሞ ያልፋል፡፡ ስራውም ዘመን ተሻግሮ ሲተርከው ይኖራል፡፡ በትውልድ የቅብብሎሽ ሰንሰለት ማጥበቂያ ቀለበት ሆኖ ትናንቱን ከዛሬ እና ነገ ጋር ያስተሳስረዋል፡፡ ለዚህ  የሚበቁት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከስንት ሚሊዮን አንድ ሁለት ሶስት. . .

ራስን ፍልጎ ማግኘት መክሊትን መለየት በእንደዚህ አይነቱ ሕይወት የመጀመሪያው ፈተና ነው፡፡ ቀጣዩ ደግሞ በመክሊቱ ማትረፍ፡፡ እናስ፣ ስንቶቻችን ነን ራሰሳችንን ፈልገን ያገኘነው? ስንቶቻችንስ ነን በመክሊታችን ያተረፍነው? በህይወታችን፣ እድሜ ዓለማችንን ሙሉ ከራሳችን ተጣልተን ውሰጠ  ሰላማችንን አጥተን የተመሳስሎ ኑሮን ኖረን የምናልፍ ስንቶቻችን ነን? የህይወት ዓለማንና ትርጉም እንደ ውርስ ሥጦታ ተቀባብለን እያስተላለፍን ኖረን የምናልፍስ ስንቶቻችን ነን? እዚህ ምድብ ውሰጥ ቁጥራችን ይበዛል፡፡ ሁላችንም እዚህ ምድብ ውስጥ እንካተታለን፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር፡፡ ራስን መፈለግ እንደማፈንገጥ፣ በራስ መንገድ መሄድን፣ የራስን ዳናን አግኝቶ መከተል እንደ መለየት ቆጥረነው፤ ሁሉ በሚሄደበት ጎዳና እየተጋፋን፣ የራሳቸውን ዳና ፈልገው ያገኙ ጥቂት የህይወት ጀግኖች እያደነቅን ራሳችንን አጃቢ ተጓዥ አድርገን እንኖራለን፡፡  የውስጥ እኛነታችን ሲተናነቀን እያፈንን ባስ ብሎ ሲገነፍልብንም ከራሳችን እየተጣላን በብሮጭቆው እና ከጠርሙሱ ጀርባ እየተከለልን በሞቅታ እውነታው ሲፈነቅለንም በ”እኔ እኮ. . .” የምናስወጣ ስንቶች ነን?

ያሰበውን የሆነ የፈለገውን የኖረ፤ ማነው? የሞከሩ ጥቂት ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ የሆነ ግን አንድ ሰው ግን ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ነው፡፡

የመክሊት እጣፈንታው ሲፈታ የተነበበት ብዙ ነገር ነው፤ መምህርነት፣ አርታኢነት፣ ፀሃፊነት የምናውቃቸውን፡፡ በጥረት እና በድካሙ ደግሞ በስነ ፅሁፉ ዓለም ደማቅ አሻራን ያኖረ፣ ያሰበውን ሆኖ የፈለገውን ኖሮ ያለፈው ስብሃት ህይወቱን ሙሉ መርሁ “ሲምፕሊሲቲ”  ነበር፡፡ ባህርይው ደግሞ ህፃን፤ ታላቅ አእምሮ የታደለው ትጉህ እና ጨዋ ህፃን የሰባ አምስት አመት ህፃን ከሁሉም በላይ ለእግዚአብሄር የቀረበ ነበር ስብሃት፡፡ በከበደ ሮበሌ አገላለፅ፡፡

በህይወቱ ከብዕር ትሩፋቱ በላይ ብዙ ብዙ ያስተማረን ሰው ነበር፡፡ ትልቅ ተሰጥኦ የነበረው ደራሲ ነው፡፡ ከጀርባ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች አሉት፡፡ የበለጠ ሊያወጣልን ይችል የነበረ፤ለሌሎች አረዓያ ሆኖ ተስፋ የሰጠ ሰው ነው፡፡ ስብሃት፤ የቅርብ ጓደኛው ተስፋዬ ገሰሰ እንደገለፁት፡፡ ለጓደኝነት የሚመቸው፣ ስብሃት፣ ስብሃት ይገባዋል፡፡ መክሊትን ፈልጎ ማግኘትን፣ በመክሊት ማትረፍን  ያስተማረ፣ ድፍረትን ያስተማረ ሰው ነበር፡፡ ስብሃት አንድም ሶስትም ነበር እንደ አዲስ አድማስ ህብረተሰብ አምድ ፀሃፊ፡፡ አንድ ስብሃትነቱ፤ በስነ ፅሁፍ ሰውነቱ፣ በፖለቲካው እውቀቱ እና በእውቀት ሰውነቱ ሶስትነት ነበረው፡፡

ስብሃት ለፅሁፍ የተፈጠረ ሰው ነበር፡፡ መፃፍን “ፔይን ኪለሩ” ያደረገ፡፡  ስቃይ መስቀሉን ሲያስነብበን የኖረ፡፡ በደራሲ አለማየሁ ገላጋይ እይታ፡፡ ለእግዜር ቅርብ የነበረው ስብሃት ሌላው መታወቂያው ያለውን መስጠት ነው፡፡ ማካፈል አይደለም፤ መስጠት፡፡ አንድ ወቅት ያለውን በሙሉ የሰጠው ስብሃት የሚያውቁኝ አላጣም በማለት በድፍረት ከጓደኛው ጋር ታክሲ ተሳፈረ ሶስት  ታክሲ መቀየርም ነበረባቸው፡፡ ስብሃት፣ ሶስት ጊዜም የታክሲ ሂሳብ ሲጠየቁ ሶስት ጊዜም “የለንም” “ያላችሁ ስጡት” በማለት ሶስቱንም የታክሲ ሂሳብ የማያውቋቸው ሰዎች እንደከፈሉላቸው ባስታወሰውም ቁጥር እንደሚገረምበት ያስነበበን የገጠመኙ ተካፋይ የነበረው ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ነው፡፡ ከሸሚዙ ስር የደረበውን ሹራብ ብርድ ላንዘፈዘፈው አውልቆ ሰጥቶ፤ከሸሚዙ ስር ጋዜጣውን ደርቦ ወደ ቤቱ፡፡ ከዚህ በላይ ለእግዜር መቅረብ እንዴት ይሆን?

ማንንም መምከር አይፈልግም ሁሉም ሰው በራሱ መንገድ እንዲሄድ የሚያበረታታ ሰው ነበር፡፡ ምከረኝ ብሎ አጥብቆ የጠየቀውንም ቀጥታ እውነታን የሚናገር ባስ ካለም በጥፊ ላስ የሚያደርግ   ሰው ነበር፡፡

እንደ ስብሃት፣ ሴት ልጅ የህይወት ጎዶሎን መሙያ፣ ማጣፈጫ ቅመም ነች፡፡ ሴት እናት፣ሴት ፍቅር እንደሆነችም በሮዝ መጽሄት ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተናግሯል፡፡

የራሱን መንገድ ፈልጎ ያገኘ፣ በራሱም መንገድ የተጓዘ የህይወት እጣውን የተቀበለ፤በጥረቱ መክሊቱን ያራባ፡፡ የብዙዎች አርአያ የሆነው ያሰበውን የሆኖ፤ የፈለገውን የኖሮ ያለፈ  የህይወት ሚስጥር በገባው መንገድ ግልጠቷን የኖረ፡፡ ስብሃት ለአብ ገ/እግዚአብሄር፡፡

“ጋሼ ስብሃት በእግዚአብሄር እቅፍ ውስጥ ገብቷል” ከበደ ሮበሌ፡፡

የህይወት ቅመሞች


በሃዘንና መከራ፤ በችግርና በሰቆቃ ጊዜያት ድጋፍ፣ መከታ፣ መከለያ፣ ጋሻ ምርኩዝና ድጋፎቻችን መሸሸጊያዎቻችን   . . . . .  በደስታችንን አድማቂዎች የጭንቀታችን እስትንፋሶች. . . የድካማችን እረፍቶች የህይወት ሐሩር ጥላ ማረፊያዎቸ . . . . የህይወት ትርጉም እውነታዎች. . . ለእሳቤዎቻቸችን ትክክለኛነት ማጠየቂያዎቻችን. . . ለጣዕምና ትርጉም የለሽዋ ህይወት ጥፍጥና እና ትርጉሞች. . .

የህይወት ቅመሞች፡፡

ሕይወት ምንድን ናት ዓላማዋስ ? ለእኔ የሕይወት ዘመን ጥያቄዬ ነው፡፡ ግን ህልውና ተችሮን ስንፈጠር ከሆነ ህይወት ምንጭ ስንፈልቅ፤ መኖር በሚባለው የህይወት ጅርት እየፈሰስን በመስኩ እየተገማሸርን፤ ቁልቁለቱን እየተዳፋን፤ አቀበቱን እንጠማዘዛለን፡፡

ሕይወት እና መንገድ

መሄድ መሄድ መሄድ. . . .

መውጣት እና መውረድ. . .

በቁልቁለቱ ስንዳፋ ህይወትንና ዓላማዋን እንደ እንደቁልቁለቱ እየበየንን፤ከመስኩ ስናርፍም ብያኔያችንን እያሳረፍን፡፤ አቀበት ገጥሞ መንገድ ሲያስለቅቀን የህይወትንም ብያኔ እንዲሁ  እየለቀቅን እየቀየርን የመኖርን ጅረት ዞረን እንቅላለን፡፡ ከምንጭ ወጥተን በመኖር ጅረት ፈሰን ከማብቂያው ምንጭ መልሰን እንጠልቃለን ፡፡ በየመሃሉም የምንሆነውን እንሆናለን፡፡ ህይወት ሁኔታዊ በዚያው መጠን ቅፅበታዊ፡፡ ያለፈውን ትዝታ አድርገን የመጪውን ተስፋ ሰንቀን በዚያ ተስፋ ግን ቅፅበትን እንኖራለን፡፡ የገባኝ ህይወት ይህ ነው፡፡ ቅፅበት፡፡ ቅፅበቷን የምናልፍበትና የምናሳልፍበት፡፡ ከህይወት ምንነት በላይ ትርጉም፤ ከህይወት ዓላማም በላይ ግብ ነው፡፡ ያችን ቅፅበት በፍቅር፡፡ የህይወት ትርጉም ፍቅርና ቅፅበት ሆነ ማለት ነው፡፡

ህይወት ቅፅበት ቢሆንም በቅፅበቷ የማንገፋው ጋራ የለም፡፡ እናም ታዲያ ለህይወት ዳገት ምርኩዝ፣ ለተዳፋቱ ድጋፍ. . . አቀበት ያለ ምርኩዝ መግፋት ምንኛ ፈታኝ ነው? ያለ ድጋፍስ ቁልቁለት ምን ያህል አስቸጋሪ ነው?

በመውጣት መውረዱ የህይወት ምጥጥኖሽ፣ሚዛን ልኬቶች አሁንም የህይወት ቅመሞች፡፡ የህይወትን ዳገት በተሰበረ ቅስም፣ በላሻቀ ሞራል መግፋት አስቸጋሪ ፈታኝ  ባስ ሲልም የመጨረሻዋን ህቅታ የሚጠይቅም ይሆናል፡፡ ለዚህ ግዜ ታዲያ ማለፊያ ድልድይ፣ ማረፊያ መስክ ድጋፍ ምርኩዝ በህይወት የሚያስፈልግን፡፡ የህይወት ቅመም፡፡

ህይወት መልካም ናት፤ ከነግሳንግሷ፡፡ ህይወት ውብምናት ተለዋዋጭ ልይዩ፡፡ በህይወት የተቃራኒ ጎኗ፣ ደስታ፣ ሃሴት ተድላ . . . ለዚህም ታዲያ የይህወት ቅመም. . . ደስታን ለብቻ መግፋት ይቻል ይሆን? አቅፈን የምንስመው፣ ጮኸን የምናስደነግጠው፣ አብስረን የምናፍነከንከው ለደስታችን አድማቂ ቀለም፣ አጣፋጭ ቅመም . . . .ለህይወት፡፡

ሕይወት ልይዩ ናት፡፡ ይህም አንዱ ቅመም፡፡ የህይወት መንገዱ አንድ ፣  መድረሻው አንድ፣  ስሌት ቀመሩም አንድ ቢሆን ኖሮ . . . ሕይወት ማስጠሎ ፡፡ በመኖር ጅረት ስንፈስ በማናውቀውና  በማይገመት ሂደት ዳና እየፈጥርን በተተለመው የህይወት መንገድ ስንፈስ ካሰብነው ስንደርስ ግብ የመታን የህይወትን ትግል ያሸነፍን ሲመስለን እንደገና አዲስ. . .  አዲስ. . .  አዲስ. . . ህይወትን ክለሳ፡፡ የህይወት ቅመም. . . .

ዑድቱን ጠብቆ . . . ሕይወት ይቀጥላል በምህዋሩ ይዞራል ቅመማት ባይኖሩስ ምንኛ ያስጠላል. . .

የእልቂት መባቻ

ሰማዩ ኮለለ

ፍንትው ጥርት አለ

ጨረቃዋም ነጣች

ብስራት ንግርን አለች

ማዕበል ተነስቶ

ዓለም ተናወጠች

አመዳይ ወረደ

ምድሪቱም ገረጣች