ግራ ገብ፤ ተዘባርቆ ኑሮ

ተመስገን ነው የነገሮችን ተዘባርቆ ተላመደን ተዘባርቆ ኑሮን መኖር ከጀመርን ሰነባብተናል ግራ መጋባትንም ተላምደናል፡፡ የማይለመድ ነገር ምን አለ? ኑሮን ለነዋሪዎች ብለን እንኖራለን፡፡ የት እንዳነበብኩት ትዝ ያማይለኝ አንድ ፅሁፍ ያሯሯጩ ፀሎት “ፍጥነቴን ጠብቅልኝ” ይላል፡፡  ዋናውን ሯጭ ለሪከርድ ወይም ለተሸለ ሰዓት እያሯሯጠ ፍጥነቱን ፈጣሪው እንዲጠብቅለት የሚፀልው ጸሎት፡፡ እኛም ነዋሪዎች የሚኖሩትን ኑሮ ማጀብ ሚያስችለንን የኑሮ ፍጥነታችን አንዳይገታ በተመሳሳይ ተስፋ ቆርጠን እንዳንወጣ የኑሮ ግሽበቱ ዙር እንዳይከር፣ በአዙሪቱም ከህይወት የዙር መም እንዳንገፈተር ተመስገን እያልን እባክህ የህይወቴን፣ የኑሮዬን ፍጥነት ጠብቅልኝ ጸሎት እያደረስን ሰንኖር ስንኖር ስንኖር ስንኖር . . . ይህው ለመድነው፡፡ ተመስገን እንበል እንዴ?

ተስፋ ማጣት ክፉ ነው፤ የማይጨበጥ ተስፋ ደግሞ አስከፊ ነው፡፡ ሁለቱም የህይወትን ትርጉም ያዛባሉ፡፡ ሰፊው ህዝብ በግልፅ በሁለቱ ምድብ ተከፍሏል፡፡ በሃገራችንም ብዙ ልዩነቶች ስላሉ ሁለቱ እምብዛም አያስደንቅም፡፡ “ልዩነት ውበት ነው” እየተባለ ሀገራዊ መፈክር ሆኖ በብሄራዊ ሞቅታ በሚዜምበት ሃገር ሁለት ዓይነት ብቻ ማስቀመጤ ያስወቅሰኝ ይሆን እንዴ? ለነገሩ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉን. . . አይታክቴው ልማት ብልፅግና እድገት፣ ሰብል አዝመራ ህንፃ ግንባታ . . . . ድህንት፤ የከፋም ድህንት ፣የሚበላ የሚያባላ ፣ባዶ እግር መንገድ ድንግርግር ውል አልባ ቁጥሮች፣ ባለ ብዙ ቀዳዳ ብስ ስልቻ፣ በዚህም በዛም ብን ብን ፣ ብን ብን ፣ ብን ብን ብቻ በዚህም በዚያ፡፡ የልማት ሰራዊት፣ ሙሰኛ ፀረ ልማት፣ ፅንፈኛ ጎጠኛ፡፡ ብዙ ልማት፣ በቃላት ልማት፣ በቪዲዮ ልማት፣ እድገት፣ ቀዳሜነት፣ ዘርፈ ብዙ እደገት እንዲው ይህ ነገር ግን ዳገት ነው የሆነው፡፡ መውጣት ያልቻልነው አቀበት፡፡ አርግጥ ነው እድገት አለ፡፡ እርግጥ ነው ልማት አለ፡፡ ፎቆች ይበቅላሉ፣ መንገዶች ይዘረጋሉ፣ ውድና ውብ መኪኖችም በነዚሁ መንገዶች ላይ ይሽከረከራሉ፡፡ አለ የተባለው ሁሉ አለ፡፡ ዋናው ማመን ነው፡፡ እመን ይደረግልሃል ነው፡፡ የሃገራችን  እድገት በእምነት የሚገለጥ እና ላመኑት ሁሉ የሚሆን የሚደረግ ነው መሰለኝ እንደቃሉ፡፡

እድገቱ በቁጥር ሲሰላም ጨምሯል፡፡ ነጋዴው፣ ሰራተኛው፣ በላተኛው፣ መጠጥ ተርቲመኛው ሁሉ አድጎ አድጎ አስራ አንድ በመቶ አደግን፡፡ በቋንቋው ዘርፍም በቃላትም አንዲሁ   በመዝገበ ቃላት ያልሰፈሩ፣ በጥራዝነጠቅ የሚዘመሩ፣ በሆበል የሚደረደሩ፣ ከአንድ ርዕዮተ ዓለም መፅህፋ ተቀድተው ወደ ሀገርና ተመልሰው ከላይ ቤት የተወረወሩ . . . ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጠባብ፣ አደገኛ ቦዘኔ፣ ትምክህተኛ፣ አድሃሪ፣ ሽብረተኛ ፅንፈኛ፣ ልማታዊ፣ አክራሪ፣ ፀረ ልማት፣ የልማት ሰራዊት  ወዘተ . . . መቶኛ ያልተሰላ በስታትሰቲክስ ያልተደገፈ የቃላት እድገት . . . .

በርካታ ቤተ እምነቶች አሉን፡፡ መስጂዶች እና መቅደሶች በብዙ ተገንብተዋል፡፡ የህንፃቸው ውበት የሃገር እድገት መገለጫና የሃገር ገፅታ ግንባታ ረገድ ከፍተኛ ነው፡፡ ከየቤተ እምነቱ በራፍ ብዙ የወደቁ ነዳያን አሉን፤ አደግገድገው አጣፍተው ገብተው  ከሚወጡት ነጭ ለባሾች የሚጠብቁ፣ በጣም ብዙ የተራበ ሆዳቸውን እየፎከቱ በዙሪያው የወደቁ ህፃናነት፣ ጎልማሶች፣ አዛውንትና አረጋውያን አሉ፡፡ እዚየው የተፈጠሩና በተመሳሳይ በዚያው የኑሮ አዙሪት ተይዘው በዚያው የእጅ ጥበቃ ህይወት ቀለበት ተጠልፈው፣ በሰው እጅ ከሚገኝ ሳንቲም ቁራሽ መኖር ይቻላል የሚለውን ትምህርት በራሳቸው ህይወት ተምረው እዚያው ጎዳና የሚቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ ይህም አንዱ የእድገታችን ክፍልና ገፅታ ነው፡፡ ሃይማኖቶችም ለአማኞቻቸቸው ምድራዊ ሰላምን እና ሰማያዊ ተስፋን አስተምህሮ መስጠት የቻሉ አይመስሉም፡፡ ወደየ እምነት ቤቶቹ ለሚሄዱት አማኞች ሃይማኖታዊ ስርዓቶቻቸውን እና ሃይማኖታዊ ተስፋን አስተምረው እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ ከመርዳት ይልቅ ምድራዊ ስልጣን፣ ሞገስ፣ ሃብት እና ዝና ማከባት ላይ በተጨማሪም ከሰማያዊው የፈጣሪ አስተምህሮ ይልቅ ለፈጡራን ከምድር ሃያላን ጋራ ያበረ፤ የመንፈሳዊ አገልግሎቱ ቀርቶ ልክ እንደሙዚቀኛ እና የፊልም ዝነኞች “ሲሊብርቲዎች” (visibility without mind) ይላቸዋል አስተማሪዎቼ አንዱ፡፡ የግል ስብዕና ግንባታ ላይ መሰረት ማድረግ እና ተከታይን ማፍራት ላይ መሰረት አድረጓል፡፡ ሳስበው የሚገርመኝ ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶች መሰረታቸው ፍቅርና መዋደድ እንዲሁም ግባቸው ፍቅርን መስበክ ሆኖ ሳለ፤ በተቃራኒው ፍቅራዊ አስተምህሮው ላይ ማተኮር ይልቅ ግን ወሰን እና ግዛትን በማስጠበቅ “የእኔ እበልጥ የእኔ እበልጥ” እሽቅድምድም ውስጥ ናቸው፡፡ ይህም ሌላ ራስ ምታት እና ግራ መጋባት፡፡ ሌላ መዘባረቅን ፈጥሯል፡፡

ወጣት የነብር ጣት፤ ወጣት እድገት፣ ወጣት ስደት፣ ወጣት ባለሃብት፣ ወጣት ደሃ፣ ወጣት ምሁር  . . .  በየፈርጁ አለን፡፡ ወጣት ተቆርቋ ወጣት ነቋሪ፡፡ ተምሮ ተመርቆ ኮብልስቶን ጠርቦ በሚያኛት ሳንቲም ነገ ባለ ሃብት ለመሆን ተሰፋ ያነገበ . . . አማራጭ እጦት ወይም ደግሞ ተስፋ ቢስ ሆኖ ስደትን መርጦም በተገኘው ቀዳዳ እየሾለከ በረሃ የበላውን ወጣት ቤት ይቁጠረው፡፡ ኢትዮጵያዊ በሄደበት እንግልትና ስቃይ እጣ ፈንታው ይመስላል፡፡ ሳስበው ሳስበው ብዙው ነገር ተዘባርቀብኛል፡፡ ሰዉ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለው፣ ምድሪቱ የቃልኪዳን  ተስፋይቱ ምድር ነበር የምትባለው፡፡ ወጣቶቻችን አስመልክቶ የሚሰማው ሁሉ አስደንጋጭ ነው ስቃይ እግልት መከራ እናም እኔ ይህን ጠየቅሁ “ኢትዮጵያዊ ዘሩ ከቃየል ነው እንዴ?” ምነው በሄደበት ተንከራታች ሆነ አልኩኝ ለራሴ፡፡ ወደ የመን በጀልባ ሲሻገሩ የነበሩ ኢትዮጵውያን . . . በተለያ የአረብ ሃገራት፣ በየመን፣ በታንዛኒያ፣ በሊቢያ እስር ቤቶች ኢትዮጵውያን . . . እንግልት እና ስቃይ፤ ባህር እና በረሃ የበላቸው ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ወዲህ በጥቃቅን እና ተደራጅቶ ኑሮ መልካም እኖርን ነው ሃብት ንብረትንም አፍርተናል ይሉናል፡፡ በየመሸታ ቤቱ ሲታዩ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልተው ሃገርኛውንም ዘመነኛውንም ጭፋራ በአይነት በአይነት ሲያስነኩት ለተመለከተ፤ ከኢትዮጵያ በላይ ምቾት እና ድሎት የተንሰራፋበት ሃገር ያለ አይመስልም፡፡ እንዲየው ጨዋታውን ነው እንጂ ጭፈራና መጠጥ የደስታ መገለጫ ብቻ አይደለም፡፡ የመፅሀፍ ቅዱሷ ሶዶምም ከመጥፋቷ በፊት ጭፈራ ላይ ነበረች፡፡ ከአንጡራ ባለ ሃብት፣ ከምሁር ፖለቲካ ተነታኝ እስከ ተስፋ ቢስ ወጣት የሞላባት ሃገር ናት፡፡ ሌላኛው ተዘባርቆ

በሃገራችንም ፖለቲካ ችግርና ተስፋ ሚዛናቸውን መጠበቅ እያቃታቸው ችግሩ ሲያመዝን ችግር በችግር፣ ምሬት በምሬት ስንሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞቻች ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት ሃገሪቱ ከመስቀለኛ መንገድ ላይ ናት በማለት መግለጫ ያወጡ እና አብዮት ሊቀሰቀስ ይችላል በማለት መንግስት ያስጠነቅቃሉ፡፡ ስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞቻችንም ጉዳዩን በሚገባ አጢነነዋል፣ ትኩረት ሰጥተን እየሰራንበት ነው፡፡ ይሉና መጀመሪያ ከከፍተኛ ባለስልጣናቱ ከቁንጮዎቹ አንድ ለማን እንደሆነ በማይታወቀው የቴሌቭዥን ብቅ ይሉና የዋጋውን ግሽበት አረጋግተነዋል፣ የተያያዝነውን የሰላም የልማት እና የዲሞክራሲ ግንባታ ለማደናቀፍ የአክራሪዎች እና እድገታችን የማይዋጥላቸው የጠላቶቻችን ወሬ እና ስልጣንን በአቋርጭ ለማግኘት የሚፈልጉ የስልጣን ጥመኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ውዥንብር ነው የሚል ወቀሳ ያቀርብባቸዋል፡፡ (በፖለቲካ ትግል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ አንድ ፖለቲከኛ የመድረሻ ግብ ሥልጣን ነው በአቋራጭም ሆነ በሌላ መንገድ ስልጣንና ስልጣን ነው፡፡ ምክንያቱም ስልጣኑን ካላገኙት እንዴት እና የት ነው የፖሊሲዎቻቸውን ትክክክለኛነት የአመራራቸውን ብቃት እና ቁርጠኝነት ሊያሳዩን የሚችሉት? ሚገመገሙት፣ የሚመዘኑት ስልጣኑን ሲይዙት እና ስናያቸው ብቻ እኮ ነው፡፡) መሰርተ ቢስ ክስ ብለን ሊከሰሱ በማይገባቸው ነጠብ ይከሳቸውና ሃገሪቱ በፍፁም ሰላማዊ እና በማይቀለበስ የልማት ጎዳና ላይ ናት የሚል መግለጫ ይሰጣል፡፡ ላለው የቤት ችግርም የተለያየ ፓኬጅ ያለው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደረግ የቤት ፕሮጀክት ተግባራዊ ስለሚደረግ ሁሉም እንደ አቅሙ እና ምርጫው እንዲመዝገብ ጥሪ     አቅርበው ሁላችንንም ለአንድ ሰሞን አሰለፉን እንዲህ ነው ግፉ በርቱ ብለን ተመዘገብን፡፡ ፖለቲከኞቻችን ችግራችን ይጠቀሙበታል፡፡ ድህነታቸን ለሁሉም ይመቻል፡፡ ሁሉም ደግሞ ይጠቀሙበታል፡፡ ስልጣን ላይ ያሉት ፖለቲከኞቻችን እራሳቸውን እንደጠባቂ መላእክት እንዳናያቸው እና ምንግዜም ኑሮኣችን ከከፋው ድህንት በእነሱ እና እነሱ አመራር፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጄ አረ እንዲያውም ከፍ ሲልም በእነሱ እርዳታ እና ችሮታ እንደምንወጣ ይሰብኩናል፡፡ ግን አንድ አይነት ሙዚቃ፣ በተመሳሳይ ዜማ፣ በተለያዩ አቀንቃኞች እድገት ብልፅግናን ሲነግሩን ይህው ስንት አመት ሆነን፡፡ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም አስልተው አሰተውለው ስህተቱን ስህተቱን እንከን እንከኑን ይነግሩናል፡፡ ለሁሉም ፖለቲካችን ተስፋ እና ችግራችን ሚዛኑን መጠበቅ አልቻለም፡፡     ይሁና የተዘባርቆ ኑሮ

Advertisements

የዲሞክራሲ ሞኖፖል

ዲሞክራሲ በእኛ አውድ ሲታይ በብዙ መልኩ ከሌላው ዓለም ለየት ሳይል አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እኛ ከሌላው ዓለም ለየት ያልን ስለሆንን፡፡ ከታሪክ ቢሉ ታሪካችን ይለያል፤ ከባሀል ቢሉ ባህላችን ይለያል፤ በምንም ቢባል በምን እኛ ከሌሎች በጣሙን እንለያን ስለሆነም ዲሞክራሲያችንም ከሌሎች የዲሞክራሲ ባህላችን ከሌሎች ይለያል፡፡

በእኛ ሃገር የዲሞክራሲ ፉክክር ከሰማንያ ሚሊዮን በላይ የሆነው ህዝባችን ከሰማንያ በላይ በሆኑ ብሄር ተኮር እና ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ይወከላል፡፡ በግርድፉ ስናመጣጥነው አንድ ሚሊዮን ዜጎች በአንድ ፓርቲ ይወከላለሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስያሜ፣ ዓላማ፣ ትግል እና የሚታገሉበት ስርኣት አንድ ነው፡፡ የሚወክሉትም እና የሚታገሉለትም ህዝብ ሃገር አንድ ነው፡፡ አረ አንዳንዶቹ  እንዲያውም ፖሊሲ እና ስትራቴጂያቸው መሰረት ያደረገበትም ርዕዮተ ዓለም አንድ ነው፡፡ የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገረ ባለበት የመለያየታቸው ምክንያት የእኛ ዲሞክራሲ ልዩ ባህርይ ምክንያት ይመስላል፡፡ ምናልባት የእኛ ሃገሩ ዲሞክራሲ አቢዮታኛው ስለሆነ ሣይሆን አይቀርም፡፡

ተነጋግሮ መለያየት ስልጡን ዲሞክራሲያዊ አካሔድ ነው፡፡ ለአንድ ዓላማ ቆሞ አንድ ህዝብን ወክሎ፣ አንድ ቋንቋ ተናግሮ፣ አንድ አይዲሎጂ አራምዶ መለያየቱ ግን በጣም አስገራሚ ነው፡፡ በውይይት ልዩነትን እያጠበቡ ወደ አንድነት ከመምጣት ይልቅ ሆነ ተብሎ መለያየት መሰረት በማድረግ የሚሰሩ ይመስላል፡፡ ልዩነትን አስፍቶ መለያየየት ለፍርፋሪ ጥሩ ነው፡፡ ሽርፍራፊ ሳንቲም እና ሽርፍራፊ ዝናን ያስገኛል፡፡ ሽረፍራፊ ተከታይም ያስገኛል፡፡ ወገንተኝነት እና ጥቅመኝነትን በሰፊው ያንሰራፋል ለአጠቃላዩ የፖለቲካዊ እና ሃገራዊ የለውጥ ትግልም ግን መሰረታዊ እንቅፋት ነው፡፡ ስልጣን ላይ ያለው ስርኣትም ከብረት የጠነከረ አምባገነነናዊ አገዛዙን ያለተቀናቃኝ ማንሰራፈት ችሏል፡፡ ገዢው ፓርቲም እንደስትራቴጂ የግለሰቦቹ ባህረይ እና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ፓረቲዎችን ከፋፍሎ የማዳከም ስራ እየሰራም ያለ ይመስለኛል፡፡

ለነገሩ . . . አንድ አይነት አይዲዮሎጂን ሶሻሊዝምን አቀንቅኖ፣ አንድ ለውጥን ናፍቆ፣ ለአንድ ማህበረሰብ ታግሎ፣ አንድ ሃሳብን እያራመዱ አንድ አብዮት አፈንድቶ፣ አንድ ትውልድን ፈጅቷል የ1966 አቢዮት፡፡ ርዝራዡ አሁንም አለ፤ አንድ ሃሳብን እያቀነቀኑ፣ አንድ ቋንቋን እየተናገሩ በአንድ መስመር ተሰልፎ መጠላለለፍ፣ በአንድ ጎራ ቆሞ መፈራረጅ  እነሱ እና እኛ መለያየት ጥቃቅን ልዩነቶቸን ማጉላት ምን ይሉታል? አለመግባባት የሚራመድበት የተለየ ዲሞክራሲዊ የፖለቲካ ምህዳር ቢኖር የእኛ ይመስለኛል፡፡

አቢዮተኛው ዲሞክራቲክ ፓርቲ ኢህአዴግም ባመጣው ለውጥ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች እንደአሸን ፈልተዋል፡፡ ኢህአዴግም የፓርቲዎቹን መፈጠር እና መኖር ሃሳቡን ከቅን ልቡናው አመንጭቶ እና ፈቅዶ ያደረገው የእሱ ለውጥ ውጤት መሆኑን ልቡን በኩራት አሳብጦ እየተናገረ የዲሞከራሲ መገለጫ የሆነው የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ግን አመጣሁት ከሚለው እና ያለተቀናቃኝ በሞኖፖል ከተቆጣጠረው ዲሞክራሲ አንድ ስንዝር ከጋት ከንፋስ እየለካ በፖለቲካው ውስጥ እንዲሳተፉ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ምክንያቱም በእኛ ሃገር ዲሞክራሲ ስላላደገ እየተለካ ነው የሚሰጠው፤ ከተሰጠ ክልል ውጭ መውጣት አይፈቀድም፡፡ በተሰጣቸው ክልል እንደ ልብ ለሚንቀሳቀሱት እና የእንቅስቃሴ ክልላቸውንም ለሚጠብቁት ብቸኛው ጠንካራ ፓርቲ “አንድዬ” ብቻ ነው፡፡ ለሚሉት፣ ተገቢው ጥበቃ በየእንቅስቃሴያቸው ሁሉ እየተደረግ በሞዴል ፖለቲካ ፓርቲነት አንድ እና ሁለት መቀመጫ፣ በቂ የሚዲያ ሽፋን እና አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረግላቸዋል፡፡ በፖለቲካው ፉክክር ንፋሷን የሚያልፋት ግን፤ እሱ ቀይ መስመር እረገጠ፣ ጫማ መለካት ጀመረ አሁን መፈታተሽ ሊመጣ ነው፡፡ መፈታተሹ በሚዲያ ይጀምር እና በህቡእ ከውስጥ የአካሄድ እና የይገባኛል ጥያቄን በሚያነሱ ቡድኖች ፓርቲን እስከመሰንጠቅ እና በግላጭ እስከመንጠቅ ሊደርስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በጅምር ላይ ካለው እና በሞኖፖል ከተያዘው ዲሞክራሲ ባልተፃፈ ህግ ከተፈቀደ ድረሻ በላይ መውሰድም መከጀልም አይፈቀድም፡፡ ለምን ቢሉ የእኛ ዲሞክራሲ ይለያል፡፡ በሞኖፖል ተይዟል፡፡ አንድን ፓርቲ ማገድ ፈፅሞ ዲሞክራሲዊ ስላልሆነ ፓርቲውን ማገድ የግድ አያስፈልግም፡፡ ፓርቲው በዲሞክራሲውን ሞኖፖል ላይ አግባብ የሆነና ፍትሃዊ የክፍፍል ጥያቄ ካላነሳ በስተቀር፡፡ ባይሆን ከፓርቲው ቁልፍ የተባሉትን ያልሆኑትን እንዲሆኑ ይደረግና እንደስፖርታዊ ውድድር በዳኛ ውሳኔ ወደ ማረፊያ ቤት ይላካሉ፡፡

አቢዮተኛው ዲሞክራሲያችንም ፈርጀ ብዙ ለውጦችን ይዞልን መጥቶ ነበር ዳሩ ምን ዋጋ አለው ሁሉንም መልሶ ወሰደብን እንጂ፡፡ የነፃ ሚዲያ መኖር የዲሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ አሳይቶ ከነሳን ስጦታዎች አንዱም ነፃው ፕሬስ ነበር፡፡ ነፃ ፕሬሱ እንደ ክረምት አግቢ እየተፍለከለከ ቢገባም ቆይቶ እንደክረምት አግቢው አቅመቢስ ሆነ ወደቀ፣ መነሳት አቃተው፡፡ በዛው ከተለያዩ አቅጣጫ አባሮሽ እና እርግጫ በዛበት፡፡ ሰላም አደፍራሽ፣ ነገር ቆስቋሽ በሚሉ እና ሌሎችም ምክንያቶች ነፃው ፕሬስ እረቆ መሄድ አልቻለም፡፡ ከውስጥ በራሱ ምክንያት እንዲሁም ከውጭ ከመንግስት እና የተለያዩ ተፅዕኖዎች የተነሳ አመስጋኝ እና አወዳሽ የሆኑት ህልውናቸውን በሚዲው ምህዳር ውስጥ ሲያረጋግጡ ሌሎቹ በማነቆ መሃል ከነችግራቸው መውተርተር ይዘዋል፡፡ አንዱም ሲዘጋ በሌላው እየመጡ አማራጭ እና ተመራጭ ለመሆን እየጣሩ ነው፡፡ አቢዮተኛው ዲሞክራሲያችን የልማታዊነቱን ጎዳና ሲያያዝ ለልማቱ ተስማሚ አጋዥ የልማት አርበኛ መሆን የፈቀዱትን አጋርነታቸውን እያደነቀ አፈንጋጭ እና አንጓጠጭ የሆኑትንም ደግሞ በግማሽ ሜዳ እንዲጫወቱ ፈቅዷል፡፡ ላለን ልዩ የሞኖፖል አቢዮተኛ ዲሞክራሲም ጥሩ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ ለነገሩ ለስታትሰቲክስ ከበቂ በላይ የመፅሄቶች ቀጥር ሳይኖረን አይቀርም በተጨማሪም በማስታወቂያ መጣንላችሁ የሚሉን መፅሄቶች ስናስብ ትኩረታቸውን እና ይዘታቸውን ከተውነው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ግን ህልመኛ ያደርጉናል ላይፍ ስታይል እና ፋሽን ያስተዋውቁናል የአልጋ፣ የተቃራኒ ፆታን የማማለያ ጥበብ እና የኦሾን ፍልስፍና ያሰተምሩናል፡፡ አማላይ እና ፈላስፋ ያደርጉናል፡፡ ለነገሩ ምስጋና “ለታላቁ መሪ” ይሁንና የእሳቸው ህልፈት የሁሉንም መፅሄቶች ትኩረት ቀይሮታል ሀገራዊ ክስተቶችን እና ጉዳዮችን በስፋት መቃኘት ጀምረዋል፡፡ ፍቅር እና ፖለቲካን እያስማሙ ይፈትሉት ይዘዋል፡፡ ኤፍ ኤሞቻችን ብቻ ናቸው እንደወጡ የቀሩት መላሽ አጥተው ዛሬም እዛው ፈረንጅ ሃገር ናቸው፡፡

የእኛ ዲሞክራሲ ክልከላ የለውም፡፡ ማንም የፈለገውን ህግ እና ስርዓቱን ተከትሎ መጠየቅ ይችላል፡፡ ህግ እና ስርዓቱንም ተከትሎ የጠየቀ ይፈቀድለታል አዝማሚያው ታይቶ ግን ሳይከለከል ሊታገድ ይችላል፡፡ ባለፈው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያካሂዲ አስፈቅደው ቀን ቆርጠው ቅስቀሳ አካሄዱ፡፡ የሰልፎቹ ቀናት ሲቃረብ ድንነገት አቢዮተኛው ዲሞካራሲያችን ትዝ ያለው ነገር ቢኖር ሊካሄድ የታቀደው የተቃውሞ እንጂ የልማቱን እንቅስቃሴ የሚደግፍ ሰልፍ አለመሆኑ ነው፡፡ ለአንድ አቢዮተኛ ደግሞ በእራሱ ዲሞክራሲ የተቃውሞ ሰልፍ ሲወጣበት ለመቀበል የሚከብደው ጉዳይ ሆነ፡፡ የተቃውሞ ሰልፉን ወደ ድጋፍ ሰልፍ እንዲቀየር በግልፅ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ስለሆነ የሰልፉ ቀን ሲቃረብ እና ጉዳዩም እርግጥ እየሆነ ሲመጣ ሰልፉ ሊደረግበት የታቀደው ቦታ እገዳ ተጣለ፡፡ ሰልፎቹ በተደረጉበት እለትም እገዳው ወደ እገታ ተቀየረ፡፡ በእገታው አጥር ውስጥ ለሚዲያ ፍጆታ በሚውል መልኩ  ሰልፉ በካሜራ ተቀረፀ፡፡ ዲሞክራሲዊ ነውና የሰልፉ መደረግ በሚዲያ ዜና ተላለፈ፡፡ በዜና የተሰራጨ የሰውን ቁጥር በካሜራ ከተያዘው ጋር በማሰማማትም ተነገረ፡፡ ግሮስበርገ የተባለ የሚዲያ ምሁር “ነባራዊው ዓለም ሚዲያውን ይሰራዋል ልክ ሚዲያውም ዓለምን እንደሚሰራው ሁሉ” ይላል፡፡ ብቸኛ እና ቀንደኛው የሆነው ኢቲቪ ሚዲያ ይሕን አባባል በሚሰራቸው የአረንጓዴ ስክሪን ዘገባዎች ሁሉ ሊተገብረው ይሞክራል፡፡ ዘገባውን ከነባራዊው ዓለም በመነሳት ይሰራዋል ከዛም የራሱን ዓለም በቴሌቭዥኑ መስኮት ይፈጥርና ለማህበረሰቡ ያስተዋውቃል፡፡ ችግሩ ኩሽት እና ውሸት ስለሚበዛው እንዲሁም ሁሉም ዘገባዎች ላይ በተመሳሳይ ስለሚደጋገገም እና ሚዲያውም እንደዲሞክራሲው በሞኖፖል የተያዘ ስለሆነ፣ ከሌላ ገለልተኛ ሚዲያ ማረጋገገጥ ስለማንችል ወይ አምነን በሚፈጠርልን የሚዲያው ዓለም እንወሰዳለን፡፡ ይህ ከሆነ የሚዲያው ግብ ተሳከቷል፡፡ አለበለዚያም ደግሞ ስለምንሰለቸው   ልማዱ ነው እያልን እናልፈዋለን፡፡ በዚህ አካሄዱ ሚዲያው በስተመጨረሻ በሚሰራቸው ዘገባዎች ላይ አመኔታን ያጣል፡፡ የእኛም ዲሞክራሲ ልዩ ነው፤ አቢዮተኞች የሰፉልን ነው አሁንም ድረስ አቢዮቱ ላይ ነው ፡፡

ሁለት ዓመት በአዲስ አበባ

አዲስ አበባ መኖር መልካም ነው፤ አዲስ አበባ ሁል ግዜ አዳዲስ ነገሮች አታጣም፡፡ አስደሳች አሳዘኝ አስገራሚ ያልተጠበቁ ብዙ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ በአዲስ አበባ ቆይታዬ አዳዲስ ጓደኞችን ተዋውቄያለሁ፡፡ በአዳዲስ የህይወት ገጠመኝ አዳዲስ ነገሮችን ተምሬያለሁ፡፡ አዲስ አበባ መልካም ናት ወድጃታለሁ፡፡ በውስጧ ብዙ ጉድ የያዘችውን መዲናችንን አዲስን የማይወዳት ይኖር ይሆን?

ወደ አዲስ አበባ ለትምህርት እንደምመጣ ሳሰስብ በመጨረሻዋ ሰዓት ደስስስስ . . . አለኝ፡፡ ከሃገር ውጭ ለመማር ብዙ ሙከራዎችን አድርጌ ነበር፡፡ ብዙ ተስፋም ሰንቄ ነበር፤ በስተመጨረሻ ሁሉም አልተሳኩም ነበር እናም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲውም የመሳካቱ ነገር አጠራጥሮኝ ለነበር ስሜን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2004 ዓ ም የትምህርት ዘመን ካለፉት ውስጥ ሳገኘው በእውነት ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ በደስታ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ ከጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ እስከዛሬ በተለያዩ አጋጠሚዎች ከተዋወቀኋቸው ሰዎች በተጨማሪ 31 አዳዲስ ሰዎች ጋር ተዋወቅሁ፡፡ እነዚህ አብረውኝ የሚማሩት ሲሆኑ አዳዲስ አስተማሪዎች፣ የቤተመፀህፍት ሰራተኞች እና የትምህርት ቤቱ የአስተዳደር ሰራተኞች ጋርም ተዋወቅሁ፡፡

ከሰው ጋር እንደመተዋወቅ ምን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለ?፡፡ ከኣዳዲስ ሰዎች ጋር በተዋወቅን ቁጥር ኣዳዲስ የህይወት አተያይ ልምድ እና ተሞክሮ እንዲሁም ተገልጦ እና ተገልብጦ የማያልቅ የሰው ልጅ ባሕርይ መማር ያስችላለል . . .እናም ባሉኝ እጅግ በጣም ውድ በሆኑት ጓደኞቼ በተጨማሪም አዳዲስ ሰዎችን በመተዋወቄ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ትምህርት በጀመርን በአጭር ግዜ ውስጥ እንደየአካባቢችን፣ እንደየባህርያችን፣ እንደየአመለካከታችን (የፖለቲካን ይጨምራል)፣ እንደምነት እና ሃይማኖታችን፣ እንደጎሳችን፣ እንደቤተሰብ ዳራችን ተመሳስሎሽ ሁላችንም ተቧደንን – ጓደኝነት መሰረትን ለማለት ነው፡፡ ይህ ጓደኝነት በተለያዩ ወቅቶች ከላይ በተዘረዘሩት መስፈርቶች ተከላሷል፡፡ በመጀመሪያ ወቅት በፍቅር እፍፍፍ ቅቤ እንጥበስ ብለን ወደኋላ ላይ ግን ባህርይ ለባህርይ መግባባት ስንጀምር ጓደኝነታችን ተቃዛቅዞ እንደገና ከሌሎች ጋር ወዳጅነት መሰረትን እንደገናም እንደገናም እንደገናም ጉድኝታችንን ከልሰን ከላልስን ወደ አመቱ መጨረሻ ወደ ኋላ ላይ በመሰረትነው ጓደኝነት ግን ዘለቄታዊ ጉድኝት ላይ ደረስን፤ መስፈረቶቻችንን አገኘን መሰለኝ፡፡

ተማሪነትን ስንጀምር የምር ተማሪ ሆንን፡፡ የተደበቀ የተሸሸገ የድሮ የተማሪነታችን ባሕርይ መውጣት ጀመረ፡፡ አሸርጋጅ፣ አጎብዳጅ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ከኔ በላይ . . . ተመፃደቂ፣ ፀጉሩን ሚያሻሸ፣ ወሬ አመላላሽ፣ ኬሬ ዳሽ (ግድ የለሽ)፣ ጥቅመኛ፣ ሸረኛ፣ ነገረኛ . . . . ብዙ አይነት . . . ሰላማዊ እና ዝምተኛ አስገራሚ የተማሪ ባህርያት ነበሩ፡፡ የአንድአንዶቹን ፈፅሞ በዚህ ደረጃ  ያልጠበቅኋቸው ነበሩ፡፡ ልክ እንደ ትምህርቱም ደረጃ ከፍተኛ የባህርይ ብስለት ላይ የነበሩ ጓደኞቸ ነበሩን፡፡ አሁን ትምህርቱንም ጥናቱንም ስጨርስ እንደትምህርት ቤቱ የምለያቸው፣ የጓደኝነት ፅነትን ብርታትን አስተምረውኝም ጓደኝነታቸውን ፍቅራቸውን አፅንቼ የማቆያቸውም ጓደኞች አሉን፡፡ ሁሉንም ጓደኞችን ግን እንኳን ተዋወቅኋቸው፡፡

ትምህርቱን ጀምረን ገፋ ገፋ አድርገን ወደ ማህል ስንዘልቅ ግን ባህርያቶቻችን ከትምህርታችንና ከስራዎቻችን በላይ በመሆን ተፅኖ ማሳደር ጀመሩ፡፡ ተፅዕኖዎቹ ቀላለል አልነበሩም፡፡  እስከ ትምህርቱና ጥናቱ ውጤት ድረስም ተሸግሯል፡፡

በትምርት ሂደት ውስጥ የየትምህርት ርዕሶቻችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሀገራችንም ሆነ ከዓለም ፖለቲካ ጋር ዝምድናና ትስስሮሻቸው ከፍ ያለ ስለነበረው ከትምህርት ውይይቱ ባልተናነሰ በክፍል ውስጥ እናደርጋቸው የነበሩ ሃገራኛ እና አለማቀፋዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የሃሳብ ፍጭቶች እና በጣም የተጋጋሉ ውይይቶችን ሁላችንም አንረሳቸውም፡፡ የውይይታችንን የግለት ደረጃ ሲገልፁ “ከውይይቱና ከትምህርቱም ማብቂያ በኋላ ልዩነቶቻችን አንትረን አውጥተን፤ የፖለቲካ ፓርቲ የምንመሰርት መስሎን ነበር . . .” ያሉም አልጠፉም፡፡ ይህን የውይይት መድረክ ሰፍቶና ተደራጅቶ በክበባት እና በማህበራት ዘልቆ በሃገራችን ውስጥ ተስፋፍቶ ማየት ያስመኛል፡፡

በነፃነት እንወያይ ነበር፣ የሚሰማንን ተናግረን እንተነፍስም ነበር፣ የመሰለንን እናዋጣ ነበር የመድረኩ ውስንነት ነው አንጂ ሁሉን አሳታፊ ነበር፡፡ መሰል የውይይት ክበባት እና መድኮች በሁሉም ዘንድ ቢኖር ኖሮ፤ በሃገራዊ የልማት አጀንዳዎች፣ መመሪያዎች እና አቅጣጫዎች ላይ ልዩነትን ሚያከብሩ ስምምነቶች ይፈጠሩ ነበር፡፡ ከመፈራራት እና የጎሪጥ እየተያዩ እነሱ እና እኛ፣ የእነሱና የእኛ ከሚል የተቧድኖ አግላይ እና ተደናባሪ የፖለቲካ አሰላለፍ መፍትሄ ሊሆነን እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም እኛ በቆይታችን ልነታችንን አክብረን በጓደኝነት ጥሩ ጊዜን አሳልፈን ነበርና ነው፡፡

እንደጋዜጠኝነት ተማሪነታችን በሃገሪቱ ስላሉት የጋዜጠኝነት ችግሮችና መፍሄዎች ላይ አስቲ እንወያይ የድርሻችንን ሃሳብ እናዋጣ በማለት ከትምህርቱ በተጓደኝም ራሱን የቻለ ሌላ የውይይት መድረክ “ቶክ ጆርናሊዝም” በሚል በሚል ስያሜ በየሳምንቱ አርብ ጀመርን፡፡ የመጀመሪያው ውይይትም የ2004 ዓም የፕሬስ ቀንን መሰረት በማድረግ ተጀመረ፡፡ በዚህ የውውይት መድረክም ብዙ ውይይቶች ተደገርገዋል፡፡ መድረኩ ጥሩ ጅምር ነበር ግን ወስን ሆነ፡፡ በመድረኩ ብዙ ሃሳቦች ተነስተዋል፡- ማን ጋዜጠኛ መሆን አለበት? ሃገራችን የጋዜጠኝነት ችግሮች ምንምን ናቸው? ልማታዊ ጋዜጠኝነት እና አተገባበበሩ፣ ጋዜጠኝት ለዲሚክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ያለው ሚና የሚሉት ዋነኞቹ ነበሩ፡፡

አተያያቸውን እና ሙያዊ ልምዳቸውንም እንዲያጋሩን ከተለያ የሙያ ዘርፍ የተለያዩ ሰዎች በእንግድነት ተጋበዘው ነበር፡፡ እንግዳን በመጋበዙ ረገድ ከእኛ ቀጥሎ የመጣው ባች የተዋጣለት ነበር፡፡ ውብሸት ወርቅአለማሁ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነ ወላ፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ፣ ጋዜጠኛ አማረ አረጋዊ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን በተለያዩ ጊዜያት በመገኘት ያላቸውን ሙያዊ ልምድና አተያይ አካፍለዋል፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ይሆናል ያሉትን ሰጥተዋል፡፡

መታሰቢያ: ለጀመሪያውው ሙት ዓመት

በባለ “ራዕይው” መሪ እነሆ በሞት ከተለዩን አንድ አመት ሞላቸው፡፡ እኔም ይችን መታሰቢያ ትሆን ዘንዳ ፃፍኳት የህውሓት እና ኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ግዜያዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዘዳንት ኋላም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦሩ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም- አቶ መለስ ዜናዊ፤ በትጥቅ ትግል አምባ ገነኑን ወታደራዊ መንግስት አስወግደው ወደ ስልጣን ከመጡበት ከ1983 ዓም ጅምሮ እና ስለጣናቸውን በፈቃዴ እለቃለሁ በማለት ሆዳችንን ሲያባቡን፣ እኛም ደግሞ የመጀመሪያው ስልጣን አቴፈኝ ያሉ ኢትዮጵያዊ መሪ ለማለት ስንዘጋጅ፣ ያሁሉ ሳይሆን ስልጣናቸውን በሞት እንዲለቁ የሆኑት አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ አንድ አመት ሆናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በስልጣን ዘመናቸው ሙሉ ወደ አውራነት ሊያሸጋግሩ ደፋ ቀና ይሉለት የነበረው ፓርቲያቸው በውስጥ ሽኩቻ እየታመሰ ነው የሚሉ አሉባልታዎች እየተናፈሱበት አንድ ዓመት ደፈነ፡፡  ለፓርቲያቸው ጥንካሬው እና መገለጫው የነበሩት አቶ መለስ ካለፉ በኋላ “ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ . . . ”   የሚለውን አባባል በፓርቲያቸው አመራር ላይ እታየ ነው፡፡ ከእሳቸውም ሞት በኋላ “ራዕይ ማሳካት” “ቃል መግባት እና መጠበቅ” እየተለፈፈ እና እየታወጀ  በቴሌቭዥኑም፣ በባነሩም፣ በሬዲዮኑም  በምኑም በምኑም እንደሞኝ ዘፈን እየተደገመ አንድ አመት አሳለፍን . . .

በአንድ ወገን  “የአፍሩካ መሪ፣ የዲሞክራሲ አባት፣ የሰላም አምባሳደር፣ የድህነት ጠላት፣ የልማት አርበኛ ብቸኛ . . . . ” በሚሉ የሙገሳ ቃለት ሲወደሱ፤  በሌላኛው ወገን ደግሞ “አምባገነን፣ ጨቋኝ፣ ከፋፋይ . . . ” በሚል ክስ እና ወቀሳ የሚቀርባባቸው አቶ መለስ ፓርቲያቸውም እሳቸው በተለሙት ልማት የእድገት እና የዲሚክራሲ ጎዳና  በእሳቸው ራዕይ አንድ አመት፡፡ በዚህም በዛም ተጀመሩ የተለያዩ የልማት ፕሮጀከቶች በፈርጀ ባዙ ተግዳሮቶች እየተውተረተረ . . . እንደ ላስቲክ እንደ ተወጠረ ህዝቡን በተስፋ እየሞላ አሁንም “በእድገት ጎዳና” ነጠላ ዜማውን እያዜመ ቀጥሏል . . . የእኔ ጉዳይ ይህ አይደለም፡፡

እኔ ማሳየት የምፈልገው “ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር ስማቸው የሚወሳውን” አቶ መለስን ከታች ባለው ትንሽ ማሳያ ነው፡፡

 

አቶ መለስ ወደ ስልጣን ሲመጡ፡

  • በኬንያ፡- ዳንኤል ኣራፕሞይ  ከ 1978- 2002 ፕሬዘዳንት ነበሩ ከዛም ደግሞ ሞዋይ ኪባኪ ከ 2002- 2013 አሁን ደግሞ ኡሁሩ ኬንያታ  ከ2013 በሃገረ ኬንያ በፕሬዘዳንትነት ተለዋውጠው ታይተዋል፡፡
  • በጋና ፡- ጆን ደን ራውሊንግስ  ከ1993- 2001 ፕሬዘዳንት ነበሩ ከዛስ ስንል ጆን አግየኩም ኪፉር  ከ 2002- 2009 እሳቸውንም ተከትሎ ጆን አቫንስ አት ሚልስ ከ2009-2012 በጋና ታሪክ ፕሬዘዳንት ሆነው አልፈዋል፡፡ ጆን አቫንስ አት ሚልስ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በተመሳሳይ ወቅት መሞታቸው ይታወሳል፡፡ ጆን ደርማኒ ማሃል ደግሞ ጆን አቫንስ አት ሚልስ በሞት ሲለዩ ከ 2012 ጀምሮ በእግራቸው ተተክተው  ሀገረ ጋናን ፕሬዘዳንትነት በመምራት ላይ ናቸው፤ ልክ እንደ እኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንበል፡፡
  • በደቡብ አፍሪካ ፡- ኔልሰን ማንዴላ ከ1994- 1999 ፕረዘዳንት ነበሩ ከዛም ታቦይ ሚምቤኪ ከ1999- 2008 ካጋልማ ፒተርስ ሞታላንቴ  ከ2008-2009 እሳቸውንም ተከትሎ የአሁኑ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ  ከ2009 ጀምሮ በፕሬዘዳንት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአፍሪካ ወጣ ብለን ተመሳሳይ ዘመናትን በወዳጅ ሃገራት መሪ የነበሩትን ስንቃኝ ደግሞ

አቶ መለስ ወደ ስልጣን ሲመጡ፡

  • በአሜሪካ፡- ቢል ክሊንትን ከ1992-2000 በአሜሪካ ፕሬዘዳንት ነበሩ ሁለት የምርጫ ዘመንን ጨርሰው ሲወርዱ፣ ጆርጅ ዊሊያም ቡሽ ለሁለት የምርጫ ዘመን ከ 2000- 2008 አሜሪካን በፕሬዛዳንትነት መርተዋል፡፡ እሳቸውም ተከትሎም ባራክ ኦባማ አሜሪካን ከ 2008 ጀምሮ በፕሬዛዳንትነት በመምራት ላይ ናቸው፡፡
  • በፈረንሳይ፡- ፍራንኮስ ሚተራንድ ከ1981- 1995 ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ከዛም ዣክ ሲራክ ከ1995- 2007፣ ኒኮላስ ሳርኮዚ ከ2007- 2012 ፈረንሳይን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል  ቀጥሎም ፍራንኮ ሃላንዴ ከ2012 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡
  • በእንግሊዝ፡- ቶኒ ብሌየር ጠቅላይ ሚኒስተር ከ1997- 2007 ነበሩ፡፡ እሳቸውንም ተከትሎ ጎርደን ብራውን ከ 2007 – 2010፣ ዴቪድ ካሜሮን ደግሞ ከ2010 ጀምሮ ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እየመሩ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ግን ለእነዚህ ከላይ ለተዘረዘሩት የተለዋወጡ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች በሙሉ ከመንበረ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንዳሉ በየዐለ ሹመታቸው ተገኝተው አለያም መልእክት በመላክ እንኳን ደስ አላችሁ፣ ሹመት ያዳብርላችሁ ብለዋል፡፡

የማይሞላ ሕይወቴ እና የማይሞላ ሆዴ

የመጨረሻ ክፍል

አረብ ሃገር ደርሳ የተመለሰች ዘመዴ እንኳን ደህን መጣሽ እንድላት ተነግሮኝ ሄድኩኝ፡፡ እንኳን ድህና መጣሽ አልኩ መንገዱ እንዴት ነበር ቆይታስ እና ሌሎች መሰል ወደ ሃገር ቤት የሚገባ ሰው የሚጠየቀውን ጠይቄ ሳበቃ ጨዋታ ተጀምሮ የኔ ደሞዝ ተጠየቀ፡፡ ወይ ፈተና፡፡

“እንዲየው ሶስት እና አራት ሺ አይከፍሉህም” አለችኝ እንደሚከፈልኝ ምንም አልተጠራጠረችም፡፡ የጠበቀችው መልስ በደንብ እንዲውም ከዛ በላይ እንድላት ነበር፡፡ እኔ ግን “አረ ተይ ቀስ እኔ አሱን ብር ቆጥሬው አላውቅም” አልኳት እና ሳስበው የደረጃ እድገት እና የደሞዝ ጭማሪ የተጋጣጠሙልኝ ግዜ የሁለቱ ባክ ፔይመነት አንድ ላይ ተደምሮ ሲሰጠኝ እንደቆጠርኩት ትዝ አለኝ፡፡ ደሞዜ ይህ ነው፤ ብዬ የደሞዜን ልክ ስነግራት ግን የሰጠችኝ መልስ ተስፋዬን ከወገቡ ቆርጦት ያቆጠቆጠው በቅርቡ ነው፡፡

“ይህን ያህል ተምረህ፣ ሶስት እና አራት ሺ ካልከፈለሁማ ምን ዋጋ አለው? ውይ የእኛ ይሻላል” አለችኝ፡፡ በአረብ ሃገር ቆይታዋም በለስ ቀንቷት እንደተመለሰች ተሰማኝ፡፡ መማሬን እንደ ልዩ እድል እንቆጥረው ተደርጌ ነበር ያደግሁት የዛን እለት ግን መልሼ ፈተሸኩት፡፡ አሁንም ግን እድለኛ ነኝ ምክንያቱም ከእኔ ጋር ትምህርቱን ጀምረውት በህይወት ጫና የሆነ ቦታ ላይ አቁመውት ትልቅ ቦታ መድስ ሲችሉ የባከኑትን አሰብኩ እንጂ፡፡ ትምህርትን አቁመው በሌላ መስክ ተተኮሱትን ማስታወስ አልፈለገኩም፡፡ ኪሳራዬን ጎልቶ እንዲታየኝ አልፈለግሁም፡፡ ይህ የእኔ የህይወት መስክ ነው ከሚለው ከግሌ መመሪያ ጋር መጣረስ አልፈለግሁም፡፡  “ነው አይደል” ብዬ ማለፉን መረጥኩ፡፡ አስገራሚው ነገር ቀጥሎ ያነሳቸው ሃሳብ ነበር “እንዴ፣ ሀገሪቱ አድጋ የለም እንዴ? ኢኮኖሚው አድጎ የለ እንዴ ለምን ለእናንተ ደሞዝ አልተጨመረላችሁም?” አለችኝ፡፡

“ምን ብዬ ልመልስ?” መስሪቤት አለቆቼ ሚያነሱትን ልንገራት እንዴ? የደሞዝ ጥያቄ ስናነሳ ይህ ደሞዝ ችግር አይደለም፡፡ ይህ አመለካከከት ችግር ነው፡፡ ይሉናል ልበላት ይህ ደግሞ የሃገርን ሚስጥር ማባከን ነው፡፡ ለነገሩ ሃገሪቱ የጋራችን ናት ስትቆይ ሁሉም ነገር ይዘልቃታል፡፡ ይገለጥላታል አልኩና “አይ እንግዲህ የት ይቀራል? ወደፊት ይጨምሩልናል አልኳት፡፡”

ቀናቶች አለፉ፡፡ ይህች ከአረብ ሃገር የመጣች ዘመዴም እንግድነቷ አበቃ፡፡ ልክ ከእኛ እንደ አንዱ ሆና የእኛን ሃገር የኑሮ ዘዬ መኖር ጀመረች፡፡ ኑሮውን ስትጀምረው ግን የጀመረችው በስሞታ ነበር፡፡ ስሞታ እና ምሬት ግን አልበቃትም ከቀን ወደቀን ምሬቷ ጨመረ፡፡ በውሃው ታማርራለች፣ በንፅህና ጉዳይ ታማርራለች፤ ከመሄዷ በፊት ነበረውን መቀበል አቃታት፡፡ ከመሰረቱ ለመለወጥ ደግሞ አቅም ጉዳይ ችግር ሆነባት፡፡ ከዛ በኋላ ሁል ቀን የአረብ ሃገር የህይወት ልምዷን ታወጋን ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የምግቡ ውድነት፣ የልብስ ውድነት፣ ምቾት ማጣት፤ በቃ ስለ ብዙ የማይመቹ የኢትዮጵ ገፅታዎች ትነግረናለች፡፡ እኛም እንሰማትና አንቺም ትለምጂዋለሽ እንላታለን ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን የእሷ ስሞታ እና አቤቱታ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ሄደ፡፡ ድንገት ስልኬ ላይ ደውላ ተሰናበተችኝ፡፡ “ምነው ትነሽ ግዜ ቆዪ እንጂ ተረጋጊ” ብላትም አልተሸነፈችልኝ፡፡ “እዚህ ወተት እንኳ ብርቅ በሆነበት ሃገር . . . ቻው” አለችኝ፡፡ ቀድማ ብዙ ተስፋ ጥላ ቶሎ ተስፋ ቆርጣ ተመልሳ ወደ አረብ ሃገር. . .

እኔስ የት ልሂድ? የት ልድረስ? የትም አልሄድም ምክንያቱም መሄድ ስለማልችል፡፡ ለምን ሃገሬ እዚህ ስለሆነ፡፡ የእስከ ዛሬ የማይሞላ ህይወቴ እና ሆዴ ገጠመኝ ይህ ነው፡፡ አንድ ቀን ይሞላል፡፡ ማን ያውቃል?

የማይሞላ ሆዴ . . .

ክፍል አንድ

 

 

ለባለፉት ሳምንታት የማይሞላ ሕይወቴን አካፍያችሁ ነበር እስኪ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ለአንድ ሶስት ሳምንታት የማይሞላ ሆዴን ገጠመኝ ላከፍላችሁ መልካም ንባብ፡፡

“ሆድ ከፊት መሆኑ በጀን እንጂ ከኋላ ቢሆን ኖሮ ገፈትሮ ገደል ይከተን ነበር” ሚለው አባባል ሊገባን የሚችለው በደንብ ተርበን የምናውቅ ከሆነ ወይም ደግሞ ሸጋ አድርጎ ሲርበን ብቻ ነው፤ ምክንያቱም የረሃብን ስሜት ሎሬት ፀጋዬ “ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?” በሚለው ግጥሙ ቁልጭ አድርጎ እንዳስቀመጠው ሆድ ባዶው ሲሆን፣ ከኋላ ቢሆን በእውነት ይገፈትረን ነበር፡፡ የማይሞላ ሆዴን ገጠመኝ ደግሞ እነሆ

አዲስ አበባ የመጣሁበት ግዜው ሩቅ አይደለም በጣም ቅርብ ነው፡፡ “ደረቅ አይባልም ለምለም ነው” የሚባው ብለው የነገሩኝ እንጀራ የሚሸጡልኝ ሴትዮ እንጀራ አንድ ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም ይሸጡልኝ ነበር እንደ መጣሁ ሰሞን ብዙም አልቆየ ሁለትን ድፍን አደረገ፡፡ ይሁን ብለን ዝም አልን፡፡ መቼም የላጤ ቁርስ በዋነኛነት ከሚቀባ አይልፍም እና  ማር ማላታ (ጃም) የሃገር ውስጥ ከአስራ ሁለት እሰከ  አስራ ስድስት ብር የውጭውን ደግሞ ከሃያ አምስት አስከ ሰላሳ እገዛ ነበር፡፡ እነዚህ ዋጋዎች  የኢኮኖሚያችን እድገት መገለጫ በሆነው የዋጋ ንረት በአስደናቂ አክሮባት ተገለባብጠው ከላይ ሲወጡ የሃያዎቹ ሃምሳ ምናምን ስልሳ እና ለሰባ ፈሪ፤ የአስራዎቹ ደግሞ ሰላሳ ምናምን እና አርባን ከዘለሉ ብዙም አልቆዩ አሁን በቅርቡ ነው፡፡ አንድ አመት ብቻ

“እትየ እገሊት እንጀራ ‘ውሻ በቁልቁለት አይጎትተውም’ ከእሳቸው ግዙ” የሚባልበት ዘመን እንደ ቀልድ ሹልክ ብሏል፡፡ የአሁን ግዜውን ግን አይደለም ውሻ በቁልቁለት ንፋስ በዳገት እያውለበለበ ሳያነሳው አይቀርም፡፡ ልክ እንደ እንጀራው ነው ዋጋው እየተውለበለበ ካናት የተሰቀለው በአጭር ግዜ ነው በሁለት እና በሁለት ከሃምሳ መሃከል ሲዋልል ቆይቶ ለክረምቱ እረፍት ቆይቼ ስመለስ ነው በአንዴ አራት ብር ሆነ፡፡ ሁን ተብሎ የሆነ፡፡ በኢኮኖሚው እድገት ይህ ሁሉ ጨመረ እሰየው ነው እድገትን የሚጠላ የለምና ሁሉ ሲጨምር ሁሉ ነገር ሲያድግ እንዴት ነው ደሞዝ በዚህ አስደናቂ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ እንደ ኢኮኖሚው በሁለት ዲጂት አስራ አንድም ባይሆን እንዲየው በነጠላ በሆነ በመቶኛ ማደግ ያልቻለው? የሁሉም ነገር ዋጋ ጨመረ ግን የሚገርመኝ እኔ ዋጋ እየጨመሩብኝ የምገዛቸው ሰዎች ትርፋቸው ጨምሮ ህይወታቸው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማየት አልቻልኩም፡፡

ሱቆቹም እንደዚያው ናቸው፡፡ ዛሬም ከላይ መስኮት ከስር መግቢያ በሩ እነዚህ ሱቆች ውስጥ ያስተዋልኩት ለውጡ ቢኖር “ደረሰኝ ካልተሰጠዎት በቀር ሂሳብ እንዳይከፍሉ” የሚል ማስታወቂያ ብቻ ነው፡፡ ማሽኑ ስላልደረሰ ለግዜው ደረሰኝ የሚሰጥ ባለ ኪዎስክ የለም፡፡ እንጀራ የሚሸጡልኝ ሰዎችም ቢሆን ቤታቸው እንደዚያው ነው፡፡ ቤቶቻቸው የተዛዘሉ እና የተዛዘኑ ናቸው፡፡ አንደኛቸው ቤት እስከመጨረሻው ሲከፈት የሌላኛቸው አስከመጨረሻው የሚዘጋ፡፡ የኑሮን ብርድ እና ቁር ለመከላከል የተጠጋጉ የተፋፈጉ፡፡ አንደኛቸው ሲያስነጥሱ ሌላኛቸው የሚያለቅሱ፡፡ ከአንደኛቸው ቤት ሲንኮራፋ ሌላኛቸው የሚቀሰቀሱ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቤቶች መሃል ከእኔ ወፈር ያለ ሰው ለማለፍ ቢሞክር በአየር እጦት የሚታፈነብት እና የሚጨነቅበት ሁኔታ ነው የሚኖረው (ይህ አገላለፅ የተኮረጀ ነው)፡፡ ደግነቱ በአቅራቢያቸው የሚያሳጣቸው ፎቅ የለም እንጂ እነዚህ ቤቶች ወዳታች ለሚመለከታቸው መሰረታቸውን ከአናታቸው ጀምረው ጣራቸውን ከስራቸው አድርገው የጨረሱ ነው የሚመስለው፤ ለንፋስ መከላከያ ከዛገው ጣራቸው ላይ የቆለሉት ድንጋይ ተጭኖ ከምድር በታች አለመስረጋቸው በራሱ የኛ ሰፈር ቤቶች ብርቱ ያሰኛቸዋል፡፡

እነዚህ ቤቶች አጥር የላቸውም ግን ብዙ በር አላቸው፡፡ “መንጩ” የሚሰሩ የሚሹለከለኩበት፡፡ እርሰዎም ከገቡ ለመውጣት ግር ቢልዎትም በመሪ ወደ ለመሄድ አሰቡበት አቅጣጫ ግን በአጭሩ የሚወጡበት ብዙ አማራጭ ይኖርዎታል፡፡ አጥር በሌለበት በሩ እንዴት ተሰራ? የሚል ጥያቄ ከነሱ መልሱ ቀላል ነው ቤቶቹ እርስ በእርስ በመጠጋጋታቸው ሸጋ አጥር ሰርተዋል በመካከላቸው ለመተላለፊያ የሚተወው ክፍተት ደግሞ በር ሆኗል፡፡ እንግዲህ እኔም እንጀራ ለመግዛት ወደ በቀረበኝ በኩል ጎራ እላለሁ ወደ አሰብኩት ቦታ ለመሄድም በሚቀርበኝ በኩል ሹልክ እላለሁ፡፡

አወይ ኢትዮጵያ ሃብታም እና ባለፀጋ ብቻ የሚኖርባት ደሃ የደሃ ሀገር ይሏታል እንጂ በእውነቱ ኢትዮጵያችን የእኛ የድሆቹ አይደለችም፡፡ ሲጀመር ለነገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ድሃ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ሰው ሁሉም ዜጋ ተገዶ ሃብታም ሆኗል፡፡ የሃብታም ሆነሃል  ተብሎ የተነገረውን አምኗል፡፡  አንድ ሊትር ውሃ በሰባት እና ስምንት ብር፣ ወተት ግማሽ ሊትር አስር ብር ገዝቶ ይጠጣል፡፡ ምግብ ሳይበላ ስለማይኖር በውድ ገዝቶ ይመገባል፡፡ እድገቷ እና የእድገቷ ፍጥነት በመላው የዓለም ሚዲያ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል እንደ ሮኬት ተተኩሷል ሁለት ሁለት ዲጂት በያመቱ ያድጋል፡፡ ዘንድሮ ቀነሰ አሉ መሰለኝ እንጂ፡፡ ይህ ሁለት ዲጂት እድገት ታዲያ በተቃዋሚዎች እና በባለሙያዎቹ ዘንድ ሁለትነትን ሳይሆን ሁከትን ፈጥሯል፡፡ እኔማ ምኑን አውቀዋለሁ ባሉኝ እሰማማለሁ፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል ይህው መንገዱ፣ ይህው ህንፃው ሲሉኝ አዎ እውነት ነው፤ ህንፃውም ተገንብቷል መንገዱም ተሰርቷል እላለሁ፡፡ ይህ የማደግህ ምልክት ነው ሲሉኝ አዎ አድጌያለሁ እላለሁ፡፡ ግን ኪሴ ባዶ ነው፡፡ ኑሮዬ እንደ ማንኛውም ደሞዝተኛ ከልደታ እስከ ባዕታ ተዝናንቼ እኖራለሁ፡፡ የባዕታ ጀንበር ስትጠልቅ ቁዠማ እጀምራለሁ፤ በመግስቱ ፀሃይቱ ስትወጣ እንደ መናኝ መነኩሴ ከምግብና ከውሃ እየራቅሁና እተቆጠብሁ የፀሎት ኑሮዬን እጀምራለሁ፡፡ የኔ ህይወት ይህ ነው፤ ልደታ ስትመጣ አቤት የእኔ ፌሽታ፡፡ ከማግስተ ባዕታ ጀምሬ ወደ ፆም እና ፀሎት እመለሳለሁ፡፡ ቴሌቭዥኑም ከምሁሩም፣ ከነጋዴውም፣ ከነዋሪውም ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምስክር በማቅረብ እድገቴን ያረጋግጥልኛል፡፡ ወይ ኢትዮጵያ . . . አብስተራክት፡፡

የማይሞላ ሕይወቴ . . .

የቤት ኪራይ ጉዳይ 

ክፍል ሦስት

ወይ አዲስ አበባ . . . ቤት ለመከራየት ስንቱን የሸገር ሰፈር ተሻገሬያለሁ፤ አቤት ደላላ . . .  ቤቱን በምላሱ ሲያሰማምረው የቤቱ ውበት፡፡ የሁሉም ማለት ይቻላል የቤት አከራይ ደላሎች የመጀመሪያው ጥያቄ  “ስንት ክፍል ነው የምትፈልገው? ከዛም እስከ ስንት ትችላለህ?” የልብ ትርታን አድምጦ ሲያበቃ  “ለጊዜው እጄ ላይ ያለው  . . . ” ይላችኋል፡፡ አይነቱን ተናግሮ “ከሆነህ ናና እየው” ይጋብዛችኋል፡፡ በዚህ መልኩ ብዙ የኮምሽን ሰራተኞች ጋር ተዋውቄያለሁ፣ (የኮምሽን ሰራተኞች ደላሎች ራሳቸውን የሚጠሩበት ስም ነው፡፡) ስንት ሰፈርስ፣ ስንት ቤትስ ቆጥሬያለሁ መሳላችሁ፡፡ “እዚህ /በአቅራቢያው ያለ ታዋቂ ምልክት ያነግረኝና/ ከእሱ በላይ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ፣ መንገድ ዳር፤ እንዴት ያለ ቤት መሰለህ ሳትቀደም ቶሎ ብትይዘው ጥሩ ነው፡፡” እየተባልኩ የሄድኩባቸው ሰፈሮች በሙሉ ከዋናው መንገድ ተገንጥሎ በሚገባ መንገድ በትንሹ ሃያ እና ሰላሳ ደቂቃ ያስኬዳሉ፡፡ እንደተባለውም ግን  ተገንጥሎ ከሚገባው መንገድ ዳር ናቸው፡፡ “ርቀቱስ?” ብዬ ስጠይቅ “ውይ ደሞ ለዚህች” ደግሞ በዚህ በኩል ወደ አንደኛው የሰፈሩ አቅጣጫውን እየጠቆመ “በዚህ በኩል ማቋረጫ አለው፡፡” ይለኛል  “ለምሸት አይመችም” ስለው እንኳ “ለማታ ነው? መንገዱ ሁሉ ሰው ነው፡፡ ሰዉ ሲሄድ ነው ሚያድረው፤ የመንገድ መብራትም አለው፡፡ አረ አያስፈራም” ይህን ሁሉ ምክንያት እኔ በጨዋ ሁኔታ ቤቱ ላለመፈለጌ ምክንያት ነው፡፡  ደላላ ደግሞ ቤቱን  ለማከራየት እና የደንቡ ከእኔና ከአከራዬ እንዳይቀርበት ነው፡፡

አወይ የቤት ኪራይ . . . .

እውነት እውነት እላችኋለው ቤት ላለው፣ መኖርስ አዲስ አበባ ነው፡፡ እውነቴን ነው፡፡ አዲስ አባበ ያለ ቤት ከልቡ ቤት ነው፡፡ ምን የማይሆነው ነገር አለ? ቢያከራዩት ይከራያል፣ ቢሸጡት ይሸጣል፣ ቢያሲዙት ይያዛል፤ እንዲየው ያረጉትን በጥሩ ዋጋ ይሆናል፡፡

መጀመሪያ የተከራየሁት ኦርጂናሌ ፎቅ ነበር፡፡ በጣም በርካሽ፡፡ ሃገር እስክለምድ እና እንግድነቱ እስኪለቀኝ ዘመድ ቤት ወጣ ገባ ማለት አበዛ ስለነበር በተከራየሁ በመጀመሪያው ወር ቤቱን የኖርኩበት በጣም ለትንሽ ቀናት ነው፡፡ የእንግድነቴ ዘመን አብቅቶ ታዲያ ራሴን ኑሮ ጀምሬ ተኦርጅናሌው /ኦርጅናሌ ያልኩት ዱሮ ፎቅ ስለ ሆነ ነው/ ፎቅ ቤቴ ገብቼ በሰላም ፈልሰስ፣ ፈልሰስ ማለትን ሳስብ ኑሮን በአግባቡ ሳልጀምር የአይጥ ደባል መጣብኝ፡፡ አመላቸው ክፋ፣ አስቸገሩኝ ቤቴን ብቻ ቢጋሩኝ ባልከፋ ነበር፤ የቤት ኪራዩ ክፍያ ብቻ ሲቀር ሁለ ነገሬን ተጋሩኝ፡፡ አልቻልኩም ጥዬ ወጣሁ፡፡

አወይ ደላላ . . .ቁጥሩ ከነበረኝ ከአንደኛው ደላላ ጋር ደወልኩ እና ሄድኩ “ምን የመሰለ ቤት አለ፡፡ እዚህ ከቁልቁለቱ ስር፣ ሰዎቹም ጥሩ ናቸው፡፡  መውጣት መግባት እንደፈለክ ባሻህ ሰዓት፣ ሁሉ ነገር እንደ ልብህ ነው፡፡ ብታመሽም አያሰጋህ የፌደራል ፖሊሶች ካምፕ ጎረቤትህ ነው፡፡” አለኝ፡፡ የፌደራል ፖሊሶችን እንዴት እንደምፈራቸው አላወቀ፡፡ በተማሪነት ዘመኔ ለእነሱ ጥሩ ትዝታ፣ ልምድም ሆነ ገጠመኝ የለኝም፡፡ ይህን እየነገረኝ የምለቅበትን ምክንያት እየጠየቀኝ ወደ ነገረኝ ቤት አዘቀዘቅን፡፡ ቤቱን ሳየው ለክፉ አይሰጥም ግን እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ የጠሩልኝን የቤቷን የኪራይ ዋጋ ብሩን በባለ አንድ ብር ኖት ዘርዝሮ ቋሚና ማገሩ ላይ ቢደረድሩት ጣሪው ሲቀር ቤቱን መገንባት ይችላል፡፡ አሰብኩ አሰላሰልኩ አወጣሁ አወረድኩና አይጥ ሳያስወጣኝ በፊት ፎቅ ቤቴን ለቅቄ ከምድር ወረደረኩ፡፡ እቃዬን አስገበሁ፡፡ አልጋዬን ሳስገባ ቤቷ ሞላች ቀሪውን የሚወሸቀን አልጋ ስር ወሽቄ የሚንጠለጠውን ከግድግዳውም ላይ አንጠልጥዬ ገባሁ፡፡ እኔ ለሰፈሩ አዲስ፣ ሰፈሩም ለእኔ አዲስ፤ ግቢውም አዲስ ነገር ሁሉ አዲስ እንግዳ ሆነብኝ፡፡ በጣም ብዙ አዳዲስ ነገሮች ጋር ራሴን ማለማመድ ተያያዝኩት፡፡ ቀን ሰላም የነበረው ቤቴ አመሻሹ ላይ ችግር መጣበት፤ ለካስ ለእኔ ያከራዩኝ ከዋነኛው ቤት አንደኛውን ክፍል የውስጠኛውን በር አሽገው፣ በውጭ በኩል አዲስ በር ከፍተው ነው፡፡ ክፍሊቱን ለማስዋብ የተለጠፈባት ወረቀት በሩን እንዳላስተውለው ጋርዶኝ ነበር፡፡ ማታ ቴሌቭዥን ሲከፈት ምስሉ ብቻ ቀረብኝ፡፡ በእዚች ክፍል በኖርኩባቸው አስራ አምስት ቀናት ቴሌቭዥን እና ፊልም ሲከፈት ምስሉ ሲቀር እኔ ቤት፣ ሙዚቃም ሲከፈት ውዝዋዜው እና ክሊፑ ብቻ ነበር የሚቀርብኝ፡፡ እሺ ይህንንስ ልታገስ፣ እኔ የቤታቸውን አንድ ክፍል ተከራየሁ እንጂ ከቤተሰባቸው አንዱ አባል አልሆንኩ የቤተሰባቸውን ምስጢር እና የውስጥ ጉዳይ የምሰማው፣ በምን ምክንያት ነው? ከሚያስቡት ወጪ የቤተሰቡ ጉዳይ ምንም ሳቀረኝ ከቤቴ ቁጭ ብዬ እከታተላለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔ ጠዋት ተኝቼ ማርፈድ እየፈለግሁ እነሱ በሚነሱበት ሰዓት መንቃት ግዴታዬ ሆነ፡፡ እንደምንም ሌላ ቤት እሰከማገኝ አስራ አምስቱን ቀን ከቤታቸው አንዱን ክፍል ተከራይቼ ከቤተሰቡም እንደ አንዱ አባል ሆኜ ኖርኩ፡፡ ከዛ ቤት ከወጣሁ በኋላ ደላላ ከአንዱ ሰፈር ወደ አንዱ አዟዙሮኝ ይኸው አሁን ከምኖርበት እና በፍቅር ከወደቅሁበት ሰፈር ገባሁ፡፡

የቤት ኪራይ ጉዱ መች በዚህ ያበቃል. . .  ብዙ ጉድ አይተናል የቤት ኪራይ ሲጀምር ምን ነበር የገጠመኝ . . . የኮንደሚኒየም ቤት ነበር፡፡ በመሃል ያለውን በር ዘግታ የቤቱን አንድ ክፍል ልታከራየኝ ነው፡፡ ዋጋውም እኔ ልከፈለው የምችለው ዋጋ ስለነበር ተስማማን ችግሩ ግን አመል እና ጅራት ከወደ ኋላ ነው በብዙ ነገር ተስማምተን ስናበቃ አከራዬ ስለ ግላዊ ህይወቴ ጥያቄ ማንሳት ጀመረች፡፡ “ሃይማኖትህ ምንድን ነው” ተናገርኩ “ትጠጣለህ” “አረ በፍፁም” መለስኩ ጥያቄዋ ግን አሁንም ቀጠለ “ታጨሳለህ” “አልፎ አልፎ” ልበላት  አሰብኩት ግን ደግሞ በቤት ፍለጋ የተንከራተትኩትን ሳስበው የግድ ጨዋ መሆን እና የራሴ ህይወት ሳይሆን የሌሎችን  ምርጫ መኖር ግዴታዬ መስሎ እየተሰማኝ “አይ አላጨስም” ብዬ መለስኩላት ግን የምፈልገውን ህይወት ልኖረው ነው ላልኖር ነው? ገና ሳልከራይ እንዲህ ቁጥጥር ከበዛ ቤት ስገባማ . . . ሳስበው ሳስበው አስጠላኝ እና ቤቱን ተውኩት፡፡

አያልቅበት ደላላ ሌላ ቤት ለማየት ሌላ ሰፈር ይዞኝ ሄደ፡፡ ስለ ሴትየይቱ አመለሻጋነት አውርቶ አልበቃውም  ስለ ሰፈሩ ሰላማዊነት እያወራኝ ስለቤቱ ፅዳት እና ግቢው እያወራን ከተባለው ቤት ደረስን ያለኝ እውነት ነው፡፡ የግቢውን በር ዘለግ ላለ ጊዜ አንኳኳን ሴትይቱ መጥታ ከፈትች ቤቱን ለመከራየት እንደመጣሁ ነገራት፡፡ ከደላላለው ጋር ከዚህ በፊት ይተዋወቁ ነበር መሰለኝ ሞቅያለ ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡ ተከራይነቴ እንዳልጣማት ከፊቷ አነበብኩ “አይይ .ይ .ይ .ይ . . ለወንድ አላከራይም አለችኝ እሰከ እዚህ ሰዓት ድረስ ደላላውም የሚነግረኝ እኔም የምሰማው የቤት አከራዮች በብዙ ምክንየቶች ወንደላጤ ተከራይን ይመርጡ እንደነበር ነውና የዚህችኛይቱ አከራይ ነገር ግር አለኝ፡፡ “ምነው?” አልኳት “ባለቤቴ ከልክሎኛል፣ ወንዳላጤ አይከራይም” ብሎኛል ደላላው ስለ ፀባዬ ጥሩነት በብዙ ሊያግባባት ሞከረ ጥሩ ጥሩ ባሕሪዬን ሲነግራት እኔ በራሴ ተገረምኩ ለካስ ብዙ ጥሩ ነገሮች ነበሩኝ፡፡ መለሳለስ ጀመረች ግን አሁንም ችግሩ የባለቤቷ ጉዳይ ነው፡፡ እናም እሷም እሺ እንግዲህ  ባለቤቴን ላማክረው እና በኋላ ተመለሱ አለችን እኔና ውዱ ጓደኛዬ ደላላም ወጋችንን እየጠረቅን ተያይዘን ወደ ምኩራባችን ተመለስን፡፡ ” በቀጠሮው ሰዓት እኔና ደላላም ሰዓቱን አክብረን ሄድን ችግሩ ግን ባለቤቷ ለወንደ ላጤ ቤቴን አላከራይምን ሃሳብ እንደፀና ነበር፡፡

ዳላዬ ደላላም እንዳልከፋበት ይደልለኝ ጀመር “ምንም ችግር የለም ደሞ ለቤት አሁን አንዱ ጋር ትገባለህ ጥሩ ጥሩ ቤቶች አሉ፤ የእሷን  የፈለግነው ያው እንደነገርኩህ ባህርይዋ በጣም ጥሩ ስለሆነ ነው እንጂ ቤትማ አይጠፋም” አለኝ፡፡ ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም ይባላል እንጂ ከክርስቲያንስ በላይ ደላላ እና ቤት ፈላጊ ተስፋ አይቆርጡም፡፡ በአዲስ ተስፋ በአዲስ ሃይል በአዲስ ጉልበት ቤት ፍለጋ ከደላላዬ ጋር አዲስ ሰፈር እና አዲስ ሰው ልንቃኝ ተያይዘን የቤት ኪራይ ካጣራበት ሰፈር ሄድን፡፡ የህይወት ሁነት እና ድርጊት ጠንቅቆ የገባቸው ደላሎች ናቸው፡፡ አይጨነቁ ሁልግዜ እነደሳቁ ነው፡፡ አይከፋቸው ሁሌ ደስ እንዳላቸው ናቸው፡፡ የፈለጉትን ሳያገኙ እና ሳያደርጉ እረፍት ያላቸው፡፡ ሃሳባቸውን ለማሳካት አንድ መንገድ ቢዘጋባቸው ሌላ አንድ ሺ አንድ አማራጮችን በአፍታ ቁጭ ያደርጉላችኋል፡፡ በመሰረቱ መፍትሄ የሌለው ችግር የለም፡፡ የዚህ እሳቤ ግንዛቤ በዋነኛነት በተግባር የሚገኘው ደግሞ ደላሎች ጋር ነው፡፡ በቲዮሪማ እነ ዶክተር እንትና የተረጎሙት የሳይኮሎጂ መፅሃፍ ላይ ታነቡታላችሁ፡፡ እንዴት ሊተገበር እንደሚችልም እነዶክተር በእንትን ትምህርት ቤታቸው ይነግሯችኋል፡፡ ችግሩ ግን “እስቲ በህይወትዎ ውስጥ በተግባር እንዴት አድረጉት?” ብትሉ እነ ዶክተር በምሳሌነት የነፎርድን ታሪክ ይነግሯችኋል ወይ ደግሞ የሆነ ተረት ተረት ይነግሯችኋል፡፡ ከተረቱም ከታሪኩም መማር የምትችሉት ግን ራሳችሁን ባዘጋጃችሁት መጠን ነው፡፡ ከደላሎች ጋር ለአንድ ሳምንት ያህል አብሮ መዋል ግን አስተሳሰቧን ከነትግበራዋ ታገኟታላችሁ፡፡

ወይ የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ስንት ነገር ያሳየችኋል . . .

በራሴ እና ጓደኞቼ ብዙ ብዙ አይቻለሁ፡፡ ለድሆች ታስቦ ከተሰራው ኮንደሚኒየም ጀምሮ እስከ ግለሰቦች ቪላ ቤቶች ድረስ፣ ያስተዋለ፣ ያየኝ የለም እንጂ ያላየሁት የለም፡፡ እድሜ ለደላሎች ሁሉንም አሳዩኝ፡፡ እንዴት ደስ እንደሚሉ፡፡ ልክ ሲደወልላቸው፡፡ “እጄ ላይ የለም አሁን በእጄ ላይ ያለኝ . . .” ይሏችኋል፡፡ ስትደርሱ ይኸው የሚሏችሁ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰፈር አዲስ አባበን ከጫፍ እስከ ጫፍ ይወስዷችኋል፡፡ ብዙ ብዙ ሰው ባሕርያትን ይነግሯችኋል በተለይ ደግሞ ግለሰብ ቤት የምትከራዩ ከሆነ ስለ ባለቤቱ ወንድም ሆነ ሴት ዝርዝር መረጃ ምን እንደሚወዱ፣ ምን እንደሚጠሉ፣ ምን ሃይማኖት እንደሚከተሉ፣ የቤተሰባቸው ሁኔታ እና የቤታቸው ሁኔታ ሳይቀር ደላላው በዝርዝር ይነግራችኋል፡፡ ይህን ሁሉ ሰምታችሁ የምትከራዩት ቤት ወዶ ገብ ነው የምትሆኑት፡፡

የአንድ ቀን የኮንደሚኒየም ውሎዬን ላካፍላችሁ፤ ብዙ ቤቶችን አይቻለሁ፡፡ እድሜ ለደላላ ያላየሁት ሰፈር አልነበረም፡፡ ኮንደሚኒየም ቤቶች ሲገነቡ ታሳቢ ያደረጉት የአዲስ አበባ የመኖሪያቤት ችግርን ለመቅረፍ ደሃውን ባማከለ መልኩ ነበር የተገነቡት፡፡ ካስገረመኝ ውስጥ ግን እንደ አካባቢው ሁኔታ የቤቶቹ የኪራይ ዋጋ መጠነኛ ልዩነት አላቸው  እንጂ እንደቤቶቹ  ዲዛይን ተመሳሳይነት የነዋሪዎቹም ብዙ ነገራቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ መኪና አላቸው፡፡ ዘናጮች ናቸው፡፡ በየመስኮቱ ግድግዳ ዲሽ አንጠልጥለዋል፡፡ በደረጃው ስትወጡ እና ስትወርዱ ገርበብ ያሉ ወይ ደግሞ የተከፈቱ ቤቶች አይጠፉም እና ገልመጥ ስታደርጓቸው አይናችሁን እዛው እንደገባ የሚያስቀረው አንድ የሆነ ነገር አያጣም፡፡ ቤቶቹ ውስጣቸው በጣም ያምራል የቤት እቃው ፅዳት፣ የአንዳንዶቹ የቴሌቭዥናቸው ግዝፈት፡፡ እነዚህ ሣሎናቸውን ለቴሌቭዥናቸው ብቻ የተከራዩለት ይመስላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የትኛው ኮንደሚኒየም ትኛውን ደሃ ታሳቢ ተድረጎ እንደተሰራ ግራ ገባኝ ነው ወይስ በሃገራችን ያለው የድህነት ብያኔ ተቀይሯል፡፡ ጠላታችሁን ግራ ይግባው እኔ ይህ ጉዳይ ግራ ግብት ብሎኛል፡፡ እነዚህ ቤቶች ውስጥ በዚህ ሁኔታ የሚኖሩቱን ደሃ ከተባሉ እኔ እና መሰሎቼ ምን እንባል ይሆን?

የቤቶቹስ ኪራይ ቢሆን አይቀመስም፡፡ ጥሩ ገቢ ላለው ላጤ እና ለአዲስ ተጋቢ ጥንዶች ጥሩ ነው፡፡ ግላዊ ህይወትን መኖር ያስችላል፡፡ ግን ልጅ ላለው እና ማህበራዊ ህይወትን በሰፊው ለለመደ አዲስ ተጎራባቾቹን እስኪለምድ ትንሽ መቸገሩ አይቀርም፡፡ ለልጆች ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙዎቹ ግንባታዎች የልጆችን የመጫወቻ ቦታ ታሳቢ በማድረግ የተሰሩ አይደሉም፡፡ ባለው ቦታም የግቢው ነዋሪዎች መኪና ስለሚያቆሙበት ህፃናት ልጆች መጫወቻ ቦታቸውን ሃምሳ ሴንቲ ሜትር በማትሞላ የየቤቶቹ በረንዳ ላይ ግድግዳን ተደግፎ ከቆመው የከሰል ኬሻ እና የልብስ ማጠቢያ ሳፋ ጋር እየተጋፉ ለመጫወት ተገደዋል፤ እናም ህፃናቱ እየተጫወቱ ስትደርሱባቸው በፍረሃትና በአክብሮት ቀና ብለው እያዩ መንገድ ይለቁላችኋል፡፡ ከፍ ከፍ ያሉት ደግሞ ግቢው ውስጥ ባለው ቦታ ከመኪኖዎቹ መቆሚያ አጠገብ እግር ኳስ ይጫወታሉ (ማስታወሻ፡- ያየኋቸው ቦታዎች በሙሉ አዣራ የፈሰሰባቸው እና ባዞላ ንጣፍ በመሆናቸው ለእግር ኳስ መጫወቻነት ምቹ አልነበሩም)፡፡ የቤቶቹን ዋጋ ዞሬ ተዟዙሬ ካየሁ በኋላ አንድ ነገር ተገለበጠብኝ፣ ኢትዮጵያ በምትባል ሃገር ውስጥ ብዙዎቻችን ያላገኘነው ወይም ያላወቅነው አንድ ድብቅ ብር እንደ ቅጠል የሚሸመጠጥበት ቦታ እንዳለ ገመትኩ እንጂ፤ ለኪራይ እንደ ሚጠራው ዋጋ እነዚህ ቤቶች የሚከራያቸው ጠፍቶ በራቸውን ከፍተው ይቀሩ ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ እሰኪ እናንተ ደግሞ የልብስ መሸጫ ቡቲኮችን እና የጫማ ሱቁን ዋጋ አስቡልኝ፤ እውነት አይመስላችሁም? እኔ ይህንብር እንደ ቅጠል የሚሸመጠጥበትን ቦታ ለሚያሳየኝ እሱ ቁጭ ብሎ እኔ ከምሸመጥጠው እርቦውን ልሰጠው ውል እገባለሁ፡፡

ወይ አዲስ አበባ

ግመገማ ኢቴቪ “ጅሐዳዊ ሐረካት፤ ሽብርተኝነት”

ቦኮ ሀራም በናጄረያ፣ አሳር ዲን በማሊ፣ ሙጃኦን አበዒ እንዲሁም አዘዋድ ኢስላዊ ንቅናቄ ማግርብ እና ሳህል በረሃ አያለ ዘርዝሮ የእነዚህን ነፀብራቅ በኢትዮጵያ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡

“የጥይት ጩኸት በርክቷል፣የርስ በርስ ግጭት፣ ሁከት እና ሽብር ከሃያ ዓመታት በላይ ዘልቋል” በሚለው መግቢያ የሚጀምረው የጅሃዳዊ ሐረካት ፕሮግራም ድህነትን ለሽብርተኝነት ቅድመ ሁኔታ አድርጓል፤ እውነት ነው የራበው ሰው ለመኖር ሲል ምንም ሊያደርግ ይችላል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ የዘያድባሬ መንግሰት ከሞከረው ያልተሳካ ወረራ በኋላ በመንግስቱ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ከተመታ እና ለተፍፃሜቱም ብዙ ከተጣረለት በኋላ ፍፃሜው ሆነና ሶማልያ በርስ በርስ ግጭት፣ ሽብር እና ሁከት ውስት ከገባች ከሃያ አመት በላይ ሆኗታል፡፡  እዚህ ጋር አንድ መሰራታዊ ነጥብ ማስያዝ እወዳለሁ፡፡ ሱማሌያውን ሰውን እንደ ሰው ላይጠሉ ይችላሉ ግን ዜጋን እንደ ዜጋ ኢትዮጵያዊን ይጠላሉ፤  ለዚህም በቂ ምክንያት አላቸው፤ የቀድሞው ፕሬዘዳንት መንገስቱ ኃ/ ማርያም እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር  መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ኮለኔል መንግስቱን ለወሰዱት እርምጃ አንድ ነገር ከወቀሳ ነፃ አድርጓቸዋል፤ በወቅቱ በዘያድባሬ መንግስት መወረራቸው፡፡ በተቃራኒው ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስን ግን የወሰዱት ተመሳሳይ እርምጃ ያስወቅሳቸዋል፤ ያም ከጀርበው ብዙ ምክንያትን ይዟል ለተባለው እና እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ገና ወረራን ማሰቡ ምክንያት በማድረግ ቀድመው ሀገረ ሱማልያ ውስጥ ገብተው ስላደረሱት ጥቃት፡፡ ያም ሆነ ይህ የሁለቱም ኢትዮጵያዊ መሪዎችን እርምጃ እንደ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ብደግፍም፤ ግን ሁለቱም ወታደሪዊ እርምጃዎች ለእኛ ኢትዮጵያውያን ያተፈረፈልን ነገር ቢኖር ከጎረቤት ሀገር ሱማልያ ዜጎች ጥላቻን ነው፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ሱማልያውያንን  ያገኛችሁ እና በጥልቀት ሀገራዊ ውይይት ያደረጋችሁ ኢትዮጵያውያን እማኝ ሁኑኝ፡፡ ይህም ሱማሌያውያን በኢትዮጵያ ላይ ለሚያራምዱት አቋም መነሻ ነው፡፡

“ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ . . . ” የሚለውን ሃገራዊ ብሂል የሚያደምቅ እና አስረጂ የሆነው የሽብርተኝነት ድንጋጌ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስለ ስልጣኑ ቅንዓት ከታላላቁ የዓለም መንግስታት ድጋፍን ፍለጋ እና ለስልጣኑ አስጊ የሆኑ ድርጅቶችን አለማቀፋዊ ይዘት ባለው ሁኔታ ለማሳደድ እንዲመቸው ከነ አልቃይዳ እና አልሸባብ ጋር በመደመር ሀ) ኦነግ ለ) ኦብነግ ሐ) ግንቦት ሰባት መ) አልሸባብ ሠ) አል ቃይዳ አንድ ላይ ፈርጆ በ”ሽብርተኛነት” በመሰየም ያልታሰበት ፈፅሞ የማታወቅ አዲስ ነገርን በፖለቲካው ተቃውሞ ጎራ እንድንተዋወቅ ሆነናል፡፡ በራስ የመተማመን መንፈሱን ያጣው እና ራሱ እየፈጠራቸው ባሉ የተለያዩ ምክንያቶች ጠላቶቹ እነደበረቱበት እንደተበራከቱበት  የተረዳው ስልጣን ላይ ያለው መንግስት እድሜ ማራዘሚያ ስተራቴጂው፣ ትናንሽ እውነት ከትላልቅ ውሸቶች ጋር በማዋሃድ የፈጠራ ታሪክን ማዘጋጀት ነው አንዱ ሲሆን፡፡ ሌላው ደግሞ ህጋዊ ማዕቀፍን በማዘጋጀት በመሰል የመብት እና የነፃነት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከአለም አቀፍም ሆነ ሌላ የሲቪል ሶሳይቱ ተጠያቂነት የማምለጫ ማቋረጫ መንገድ ክፍተት ማግኘት መሆኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወገኖች እያስተቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ማንም ቢሆን ስለተነገሩን ድርጅቶች እንቅስቃሴ እርምጃዎች እውነተኛነት የሚክድ የለም፡፡ በፊልሙ የተካተተው አብዛኛው አትዮጵዊ ይዘት የተሰጠው የፊልሙ ታሪክ ግን ልብ ወለድ ነው፡፡ እናም እስከ አሁን ድረስ ግን እነዚህ ድርጅቶች በአለም ዓቀፍ ሚዲያ የምንሰማውም ሆነ የምናየው አይነት ጥቃት በመፈፀም ሃላፊነቱን እንወስዳለን በማለት እንደምናውቃቸው የዓለም “ሽብረተኛ” ቡድኖች ሲፎክሩ አላየንም፤ አልሰማንም፡፡ እውነት ነው እነዚህ ቡድኖች ብሄር ተኮር እንቅስቃሴያቸው ካስገኘላቸው ተቀባይነት አንፃር የተነሱበትን አላማ ከግብ ለማድረስ የተሸለ አቅም እና መስረት ስላላቸው ይህም በገዢው መንግሰት ጥርስ ውስጥ ስላስገባቸው “ሽብረተኛ” በመባል ተፈርጀዋል፡፡ በተገኙት አጋጣሚዎች እና ክስተቶች ሁሉ በእነዚህ ድርጅቶች ተላኮ  ሃላፊነቱን እንዲወስዱ ይደረጉና እንደ እንግሊዝኛው አባባል “እስኬፒንግ ጎት” ይሆናሉ፡፡ በይዘትም ሆነ በፕሮዳክሽን ደረጃው የወረደው ይህ ብዙው የፊልሙ ታሪክ በፈጠራ ላይ የተመሰረተው ይህ ፊልም የተሻሉ ባለሙያዎችን ጋብዞ እና አሳትፎ  ቢሆን ኖሮ በአንድ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የተሸለ ደረጃ እና ተቀባይነት ሊኖረው ይችል ነበር፡፡

በፊልሙ ውስጥ የተካተቱ የክስ ነጥቦች፡-

  1. “እስላማዊ መንግስት ማቋቋም” ይህ ክስ “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” በሚለው ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር ንግግር ይጀምር እና በማስረጃ ለመደገፍ ይሞከራል፡፡ በመርህ ደረጃ እውነት ነው፤ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው በተግባር ግን የማታይዩ ረጃጅም እጆች ከመንግስት ወደ ሃይማኖት ተቋማት ከሃይማኖት ተቋማት ወደ መንግስት እየተሰነዛዘሩ እከክልኝ ልከክልህ ከዚህ በፊት ከምናውቀው የተለየ ሃይማኖት እና የመንግስት ትስስር እና ጥምረት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስቱን ከለላ እና ሽፋን በማድረግ ስር እየሰደደ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ስለምን የመጀሊሱ ምርጫ በቀበሌ ተካሄደ? የሲኖዶሱስ ጉባኤ እና የአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫስ የባህር ማዶው እና የሀገር ቤቱ  ሲኖዶስ እርቀ ሰላም ሳይከሄድ የእርቅ ሂደቱ በተለያዩ ምክንያቶች እተደነቃቀፈ ፓትርያርክን በእጣ ሳይሆን በኮሮጆ ለመምረጥ ሩጫ እና ጥድፊያን ምን አመጣው?
  1. “ነባሩን የመቻቻል ባህል እና ሃገራዊ አንድነት” ለማጥፋት ተብሎ የተተረከው ይህው “የሽብርተኝነትን አውጋዥ እና አጋላጭ” ፊልም እሰከሚገባን ከመቻቻል በላይ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ክፉውን በሩቁ ያድርግለት እና ይህ ህዝብ ታጋብቶ ተዋልዶ ከመቻቻል በላይ ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህን አለማመመን ክህደት በቁልቁለት ይሆናል፡፡
  1. የመሰብበሰብ እና የመደራጀት ህጋዊ መብት ባለበት ሃገር በህቡዕ ወይም በስውር መደራጀት ለምን አስፈለጋቸው? ይህ ጥያቄ መልሱ አጭር እና ግልፅ ነው፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ  ለአንድ ወር ከልክለዋል እናም ወሩ እስከ ዛሬ አይለቅ ወይም ሌላ ምክንያት እስከ አሁን መልስ አልተሰጠበትም፤ መሰብሰብ ክልክል ነው፡፡ የመደራጀቱም ጉዳይ ቢሆን እንደሚወራው ቀላል አይደለም  ጣጣው ብዙ ነው፡፡
  1. “ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ” የሚለው ሌላው የክስ ነጥብ ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት የፀደቀው ከሃያ ዓመት በፊት ነው፡፡ ከሃያ ዓመት በኋላ ደግሞ ብዙ ለውጦች ተከስተዋል፣ እይታዎች ተቀይረዋል፣ አስተሳሰቦች ተሻሽለዋል፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ  የወቅቱን እውነታ እና ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ መሻሻል በህገ መንግስቱ ላይ እንዲደረግ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት ተደርጎ ሁሉም ሃሳብ ሰጥቶበት የሚቀየረው ሊቀየር ሚሻሻለው ሊሻሻል ይገባል አለበለዚያ መንገዶችን መዝጋት ተገቢ አይሆንም፡፡

 “የሽብርተኝነት ቃል

“ዳሩ ቢላል የአል ሸባብ እና የአል ቃይዳ ድልድ በምስራቅ አፍሪካ ነው” ይህው ቡድን በኢትዮጵያ ያሉትን “የሽብር ቡድኖች” በማስተባበር እና በማደራጀት ሀገሪቱን ወደ ጥፋት ቀጣና የመጨረሻ ግብ እንደሆነ የገለፀው ይህ የቴሌቭዥናችን ፕሮግራም፡፡ “ተጠርጣሪ ሽብርተኞች” በመማስረጃነት ሊያቀርብ የሞከረው ቃለ መጠይቃቸው ግን አስተውሎ ለተመለከተው እነዚህ ምስኪን ዜጎች በወከባ እና ጫና ውስጥ ሆነው እንደተናገሩት ፊታቸው ላይ የነበረው አለመረጋጋት አንዱ አስረጂ ነው፡፡ የአቡበከር አህመድ የተቀረፀው ምስል ከ33′ 57 ጀምሮ ያለው የቃለ መጠይቁ ክፍል አንድ ነገር ያሳያል፣ አቡበከር በወከባ ውስጥ እንደ ነበር ያሳያል፡፡ የብቃት ማነስ ይሁን ሆን ብሎ ኤዲተሩ እዚሁ ጋር ፍንጭ ትቶልናል፡፡ ፊልሙን ደግማችሁ ተመልከቱልኝ፡፡ ተቆርጠው በኤዲቲንግ መውጣት የነበረባቸው ድምፆች እና መሪ ጥያቄዎች በሙሉ ተቆርጠው ስላልወጡ  እነዚህ ምስኪን ዜጎች የሰጡት ቃል ነፃ ሆነው እንዳልነበር ማሳያ ነው፡፡ ኤዲተር ሆይ አውቀህም ሆነ ሳታውቅ ለተውክልን ምልክት ምስጋና ይግባህ/ሽ፡፡

አማን አሰፋ (እስማኤል) የሰጠውን ቃል እያደመጥሁ ዓይንን ዓይኑን አየሁት፤ አንደ ሰው የሚያምንበት ከተናገረ ምንም መገላመጥ ጣራ ጣራ ማየት ሳያፈልገው ፊት ለፊት እያየ ይናገራል እስማኤል ግን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንደተናገረው የተቀረፀው የቪዲዮ ምስል ያስረዳል፡፡ እንባ ያቀረሩት አይኖቹ ማረፊያ አጥተው ከጣራ ወደ ግድግዳው ግራ እና ቀኝ እየተንከራተቱ ሲናገር (ከቪዲዮው ምስል ዓይኑን አስተውላችሁ እዩልኝ) ምንም አማራጭ እንዳልነበራቸው (helpless) ትረዳለችሁ፡፡ ካሚል ሸምሱ እና አህመድ ሙስጠፋም ሆኑ ሌሎቹ በዚህ ቪዲዮ ላይ ተካተቱ ምስሎች  የቪዲዮው ብርሃን በአግባቡ ዓይኖቻቸውን እንድናይ አያደርገንም፡፡ በቀረፃው ወቅት ካሜራው ፊት ለፊት የቀረፃቸው ውስኖቹን ነበር ከፊሎቹን ከጎን ሲቀርፅ ከፊሎቹን ደግሞ ደብዘዝ ባለ በብርሃን ውስጥ ስለነበር አይኖቻቸቸው በጥላ ተሸፍኗል፡፡ በተለይም ካሚል (ካሚል ምናልባትም ጥሩ አክተር አልነበረም)፡፡ የድምፀ ቃናቸውም ሆነ የምስሉ የድምፅ ፕሮዳክሽን አንድ አይነት ነገርን ጠቋሚ ነው፡፡ ቀረፃው ስለተከናወነበት ሁኔታ የሆነ ፍንጭ አመላካች ነው፡፡ በተግባቦት ወቅት  ዓይን የቃል ንግግርን ያህል ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል፣ ድምፅ አውጣጥ እና የንግግር ፍሰትም እንዲሁ ስለ ውይይቱ ይዘት እና ሁኔታ ጠንከር ያለ መልዕክትን ያስተላልፋል፡፡ (አንደንድ እነዚህን ምስኪን ዜጎች የንግግሮችን ክፍሎችን በደንብ አድምጡልኝ ከንግግር ይልቅ የትርክት ቃና ኣላቸው፡፡ የተሸመደዱ ወይም ደግሞ የተነበቡ ነው ሚመስሉት፡፡ ETVን እንዲደግመው ብትጠይቁ አመቱን ሙሉ ይደግመዋል እና በጥሞና ተከታተሉት ትለዩታላችሁ)  ለዚህም የተግባቦት (Communication) ባለሙያዎች አግዙኝ እነዚህ ምልክቶች አንድ ሰው እውነት ያልሆነን ወይም ደግሞ ያላመነበትን ሲናገር (አይኖቹ ማረፊ አጥተው ከጣራ ወደ ግድግዳው ግራ እና ቀኝ መንከራተት መሬተረ መሬት ማየት) የሚያሳያቸው ምልክቶች ስለመሆናቸው በBarbara እና Allan Pease የተፃፈውን Definitive Body Language የሚል መፅሃፍን በአስረጅነት እጠቅሳለሁ፡፡

ካሚል ሸምሱ ከሌላ መድረክ ላይ የተናገረውን “ህጋዊ መንገድን ተክተሎ የሚሄድ ማንኛውም ሰው ምን ግዜ አሸናፊ ነው የሚሆነው” ሚለውን ንግግሩን እንደ መግቢያ በመውሰድ በቀጣይ ከምርመራ ክፍል የተከተለው ቴሌቭዝኑ ፊልም የሚያሳው ካሚልም እንደ አማን ሁሉ ካሚልም አሰገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ የቪዲዮው ምስል ያስረዳል፡፡ የቪዲዮውን ምስል ደግማችሁ ተመልከቱት፡፡

ሠለፊያ ጭማቂ ቤት ፤ የመደራጃ እና ውይት የሚያካሂዱባት ቤት ናት እንደ ቴሌቭዥኑ ማብራሪያ፤ ያ ሊሆን ይችላል ደግሞም ላይሆንም ይችላል፡፡ ሠለፊያ የሚለው ስያሜ ሆነ ብለው አስበው ለዚህች ጭማቂ ቤት ከሰጡ በተመሳሳይ ሠለፊያ እየተባለ ይጠራ የነበረው በቅርብ ጊዜ ከህትመት የወጣው ጋዜጣስ ከዚህ ቡድን ጋር ምን ግንኙነት ነበረው?  የዚህች ቤት በዚህ ፕሮግራም መካተት ለእኔ ከዚህ የዘለለ ምስል ይሰጠኛል፡፡ ይህች ቤት ከዚህ “የሽብር እንቅስቃሴ” በተያያዘ መዘጋቷ ምናልባትም መወረሷ ስለማይቀር በዚህች ቤት ገቢ ይተዳደሩ ነበሩ ሰዎች ችግር፡፡

“ተጠራጣሪ” ብሎስ “የሽብር ቡድን”ን ምን አመጣው ተጠርጣሪ የሚያመለክተው አለመረጋገጡን ሲሆን፣  የሽብር ቡድን ደግሞ ሲባል ደግሞ ፈርዶ እና ፈርጆ ከድምዳሜ ላይ መድረስን ነው፡፡ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ እና የሚጋጩ ሃሳቦችን በአንድ ላይ መሰደርን ምን አመጣው፡፡ ወይ ተጠርጣሪ ወይ ደግሞ ሽብረተኛ አንዱን ሀሳብ መያዝ እንጂ “ተጠራጣሪ ሽብርተኛ” ን  መጠቀሙ አንድ ነገር ያሳያል ይህ ፕሮግራም የተላለፈው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ሰዎች ላይ ነው ክህጉ ውጭ የሚታደጋቸው ምንም ሆነ ማንም የለም፡፡ ጥፋተኛም ሆነው ከተገኙ የሚበይንባቸው ይህው የፍትህ ስርዓት ነው፡፡ ስለሆነም ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ እና ይህም ቪዲዮ ጥፋተኛነታቸውን አረጋጋጭ በመሆን በማስረጃነት በፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የተረዱ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡትን የፍርድ ቤት እገዳ ጥሶ የተላለፈ ፕሮግራም በመሆኑ የቴሌቭዥን ጣቢያው ከዚህ በፊት “አኬልዳማ” በሚለው ተመሳሳይ ድርጊቱ የተከሰሰበት ጥፋት ላለመድገም እና እነዚህንም በህግ ከለላ ስር የሚገኙ ምስኪን ዜጎች ሁለት ትርፍ ለመውስድ ሆን ተብሎ የተመረጠ አገላለፅ ነው፤ “ተጠራጣሪ ሽብርተኛ” እና “ተጠራጣሪ የሽብር ቡድን”፡፡

አንድ፣ አስቀድሞ ህዝቡ በቀረበለት መረጃ አሸባሪ ብሎ እንዲፈርድባቸው ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  ቀድሞውም ቢሆን “ነፃ” እና” ገለልተኛ”ነቱ ላይ እምንት በማይጣልበት የፍትህ ስርዓት ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ሲባል ነው፡፡ አወይ “Evil TV” (ይህ አገላለለፅ ከዚህ ፕሮግራም መተላለፍ በኋላ በማህበረሰብ ድረ ገፆች አንዳንዶች ለቴሌቭዝን ጣቢያው የሠጡት ስያሜ ነው) ከህግ ተጠያቂነት ማምለጫ ሰርጥን ማበጀቱ ነው፡፡ ለነገሩ በቆረጣ የገባ ቡድን በሰርጥ አቋራጭ ማምለጫው መች ይጠፋዋል፡፡ ሌላው ደግሞ “የፖሊስ የምርመራ ውጤት ያመለክታል”  የሚለውም ተደጋጋሚ ሀረግ  አስተውሉልኝ፡፡ ፖሊስ ካረጋገጠ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሲገባው፣ ወደህዝቡ ሄዷል፡፡ ህዝቡ ይህን ፕሮግራም ተመልክቶ ከፍርድ ቤት አስቀድሞ ዳኝነቱን ይሰጣል፡፡ ተጨማሪው ጉዳይ ደግሞ  እነዚህ ምስኪን ዜጎች በዚህ ፊልም  ምስላቸው የቀረበበት መንገድ በቀጣይ በግላዊ እና ማህበራዊ ህይወታቸው መስተጋብር ላይ የሚመጣውን ተፅዕኖ እና ቀውስስ በጣም አደገኛ ነው፡፡ በፍርድ ሂደቱ በነፃ ቢለቀቁ እንኳ ወደ ማህበረሰቡ ተመልሰው ሲቀላቀሉ ማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው ምስል እና ስብዕና ምን አይነት  ነው?

የፊልም ፅሁፉን አንባቢውምን በሚገባ አድምጡት የሚጠራቸውም ቃላቶች ሲናገር ወጥነትእና ፍሰትም አልነበረውም፡፡ አፍሪካን አዲስ ስም ሰጥቷቷል ወይም ደግሞ እሱም እንደ ኤዲተሩ የሆነ ነገር ሊጠቁመን ፈልጓል ከዚህ በዘለለ ግን ይህ  አፉን ያልፈታ የሚመስለው አንባቢ አፍሪካ የሚለውን ቃል እንኳን በትክክል መጥራት ያልቻለ “ቃ”ን ከ”ካ” እያደበላለቀ ነው ያነበበው፡፡ የማጠቃለያ ነጥብ ይህም ፊልም በውስጡ ያዘው ምስል በእድሜ ገደብ ሊታይ ሲገባው የእድሜ ገድበ ሳይደረግበት ሁሉም እንዲመለከተው እና ሁሉም ሰው ቴሌቭዥን በሚመለከትበት ሰዓት መተላለፉ በእውነቱ በህፃናት ስነልቡና ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና እና የሚፈጥረውን ተፅእኖ በአግባቡ ተጢኖ ይሆን?

የማይሞላው ህይወቴ

ክፍል ሁለት

እኛ ሰፈር ብዙ ሱቆች አሉ፡፡ ትናንሽ የሸቀጥ ሱቆች ናቸው እንጂ፡፡ እነዚህ ሱቆች ታዲያ ለእያንዳንዱ የሰፈሩ ነዋሪ ህይወት መሟላት እና መሳካት፣ ሰው ቀምሶ እንዲያድር ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሰው እንደ ሃሳቡ እና እንደኪሱ የፈለገውን ከእነዚሁ ሱቆች ያገኛል፡፡ እነዚህ ሱቆች ውስጥ የማይገኝ ነገር የለም ከእለት ጉርስ ዳቦ፣ ብስኩት እና እንጀራ ጀምሮ እስከ የህይወት ጋሻ ተደርጎ የሚታሰበው የጉዳዩ  መፈፀሚያ ያቺን . . . ነገር በሁሉም ሱቆች ያገኛሉ፡፡ ሰው መኖር የሚችልበት ሰፈር ውስጥ ነው የምኖረው፤ በዚህም ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሰፈሬንም የወደድኳት የህይወትን ብዙ ምስጢር ስላስተማረችኝ ነው፡፡ ሰው እንዳቅሙ የሚሽቀረቀርባት ሰፈር ናት፡፡ ሰፈሬን እወዳታለሁ፡፡ በእኛ ሰፈር የኑሮ ውድድር፣ አብዛኛውን ነዋሪ ህይወት በቀዳሚነት እየመራች ትዘውራቸዋለች፤ ሕይወት መዘውሯ ከነዋሪዎች እጅ ካመለጠ እና ህይወታቸውን በራሳቸው መምራት ካቆሙ ቆዩ፣ ሰነባበቱ፡፡

ቀደምት ስልጣኔ ጮራው ሲፈነጥቅ እኛ ሰፈር ብልጭ ለማለቱ የአካባቢው ቤቶች እና ነዋሪዎች ምስክር ናቸው፡፡ ቤቶቹ መስመራቸውን ጠብቀው በሆነ ደረጃ በወቅቱ እንደተሰሩ አደራደራቸው ያስታውቃል፡፡ የድንጋዮቻቸው አጠራረብ ደግሞ እንዴት እንደሚያምር ነበር፤ ችግሩ እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች እና ፋርማሲዎች /የመድሀኒት ሱፐር ማርኬቶች/ እየተሸቀዳደሙ ነጭ፣ ቢጫ፣ ቀይ፣ ጥቁር፣ አረንጓዴ ምናምን ቀለም እየደፉባቸው ተፈጥሮአዊ የድንጋይ ቀለሞቻቸውን አጠፉት፡፡ ያም ሆኖ ግን የድንጋዮቹ አጠራረብ ውበት አሁንም ድረስ እንዳለ አለ፡፡ የተገነቡበትን ዘመን ስትጠይቁ “ዘመኑ ሩቅ ነው” ይሏችኋል፡፡ “የፋሺሽት ወረራ ጊዜ” ይሏችኋል (የዘመናችንስ ህንፃዎች ከሰባ እና ሰማንያ ዓመታት በኋላ እንዲህ እንዳማረባቸው እናገኛቸው ይሆን?)፡፡ እነዚህ የጥንት ቤቶች ታዲያ የዚያን ወቅት ጀምረው ሲሰጡ የነበረውን ግልጋሎት አሁንም ድረስ አላቋረጡም፡፡ የመጠጥ ግሮሰሪ፣ ሆቴልና ቡና ቤት ናቸው፡፡ የማን መሆናቸውንም ጭምር የሚገልፁ ስሞቻቸው ከፊት ለፊታቸው እንደተፃፉ፣ ከአናታቸው እንደተንጠለጠሉ የዘመን ቀለማቸው እና የመፃፊያ ሰሌዳቸው ብቻ እየተቀየረ እስከ ዛሬም ድረስ ከቤቶቹ አናት እንደተሰቀሉ አሉ፡፡ ቤቶቹም አላፊ አግዳሚውን፣ ቋሚ ደንበኞቻቸውን እንደ ዘመኑ ስርዓትና እንደ ወቅቱ ሁኔታ ያሰተናግዳሉ፡፡ ከእነዚህ ቤቶች አንዳንዶቹ የሚነጋለቸው ጀንበር ስትጠልቅ ነው፡፡ ጀንበር ከጠለቀች በኋላ ንጋታቸው ሲጀምር ዝምታቸውን ሰብረው፣ በራቸውን አንገርብበው በደብዛዛው ብርሃን የቤቶቹን እኩሌታ ከሚያህል ድምፅ ማጉያ ከወደ አንዱ ጥግ አቁመው በሚለቁት ሙዚቃ እያዛጉ ደመቅ መቅ ብለው የተገለበጠ ንጋታቸውን አመሻሽ ላይ ይጀምራሉ፡፡ እየሞቁ እየደመቁ የሚሄዱት እንደጨረቃ አወጣጥ ነው፤ ልክ እንደ መዐልት ጀንበር፡፡ ወደ እኩለ ሌሊት ግድም እነዚህ ቤቶች ከአቅማቸው በላይ በሰው ይሞላሉ፤ የሚለቀቀው ሙዚቃም ምትም ቤቶቹን እያውተረተረ ዝምተኛውን የሌሊት ፀጥታ ይፈታተነዋል፡፡ ጨረቃ አዘቅዘቀ ንጋት ሲቃረብ  የእነዚህ ቤቶች እና ደንበኞቻቸው ምሽት ይጀምራል፣ ጎህ ሲቀድ፣ ጀንበር ጠልቃ ድንግዝግዝ ይላል፡፡ በአልኮል፣ በሲጋራ በጭፈራ እና  (ሌላም የአጭር ጊዜ ትውውቅ እና ቆይታም ሊኖር ይችላል) የዛለ ሰውነት ደንዝዞ፤ የተዝናንቶ ምሽቱን የጨረሰ እና የቀሪውን ሰዓት ቀጠሮ እና ውል ያለውም እየተጣደፈ ተያይዞ ለእረፍት  መውደቂያ ፍለጋ . . . የተድባበ ጥላሁንን “መኃልየ መኃልይ ዘ ካሳንችስን” ለበለጠ ትንታኔ ልጋብዛችሁ፡፡  የሰፈራችን ህይወት ከካዛንችስ ጋር በመጠኑ ይመሳሰላል፡፡

አዲስ  አ . . .በ . . . ባ . . .

መሃሉ. . . አይነገር

ዳ . . . ር. . .  ዳ . . . ሩ . . .

አ. . .በ. . . ባ . . .

አዲስ እንደ ስሟ ሁሌም አዲስ ናት፡፡ ወጣ ብሎ ከርሞ ለሚመጣ አንድ የሆነ አዲስ አስደናቂ እና አስገራሚ ነገር አታጣም፡፡ ለዚህም ጓደኛዬ አማርኛውን እና እንግሊዝኛውን አቀላቅሎ “Addis is always Addis” ይላታል፡፡ አዲስ አበባ ለመኖር ምቹ ናት በተለይ ደግሞ ላለው፡፡ እኔ ይህን የምለው ሲኖረኝ ሲኖረኝ ስለምትመቸኝ ነው፡፡ የሌለኝ ግዜ ግን ያው ራሴም የለሁም እልና “ማጣትን እና ጥይትን ተኝቶ ማሳለፍ ነው” እንደሚባለው ከወደጥጋት ጋደም ብዬ ደስ ሲለኝ መፅህፍ፤ ካልሆነም የህይወቴን መንገድ የኋላውን ከፊተኛው እያስተሳሰርኩ እና እየሰናሰልኩ በማንበብ አሳልፈዋለሁ፡፡

የማይሞላ ህይወቴ እና ሆዴ . . .

አዲስ አባበ ከመጣሁ ሁለት ዓመት ሊሞላኝ ጥቂት ይቀረኛል፡፡ በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ የገጠሙኝ እና የታዘብኩት የአዲስ አበባ ህይወት ላክፍላችሁ፡፡ ፅሁፉ ትንሽ ረዘም ስለሚል በክፍል በክፍል አቀርብለችኋለሁ መልካም ንባብ፡፡

የማይሞላው ህይወቴ

ክፍል አንድ

ሰፈራችን በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ቀደምት ስልጣኔ በአቋራጭ ወደ መሃል አራት ኪሎ የዘለቀው በዚህ በኩል እንደሆነ አስረጅ አዛውንት በኑሮና በህይወት ተገፍተው በመውጣታቸው ምስክርነት ለመስጠት ባይችሉም እኔም ምስክር ባልቆጥርላችሁም አስረጂዎቼን ግን ወደኋላ አቀረባለሁ፡፡

የህይወት ልዩነት ጥግ በሰፈራችን በሽ ነው፡፡ ጦም አዳሪ አይጠፋም፤ በልቶ ተርፎትም ምግብ የሚደፋ አይጠፋም፡፡ ርሃብ አቆራምዶት የራበው ሆዱን እየፎከተ፣ ዘባተሎ ለብሶ ካርቶን አንጥፎ ጥጋት ስር ወይ ደግሞ  መሃል ጎዳና ድንጋይ ተንተርሶ ፍንድስ ብሎ የሚያድርም አለ፡፡ ሰፈራችን የደህንነት ስጋት ስላለ ይሁን ብቸኝነት በመባዛቱ ሁሉንም ሕይወት በየፈርጇ ባልንጅሩን እና አጋር እንዲፈልግ አድርጋዋለች፡፡  በጎዳና ሕይወት የከተሙቱም ሆኑ በቪላ የሰፈሩቱ እንደ ቢጤያቸው ተዛምደዋል፡፡ የአንዳንዶቹን ከገረመኝ ላካፍላችሁ፡፡ ጎዳና አዳሪውን ሳትዘነጉብኝ ቤታችውን ባማረ ግንብ አጥረው እና የብረት በር ገጥመው ሲያበቁ፤ ሃሳባቸውን እኔ እንጃ፤ በግንቡ አጥር ላይ ካናቱ የቆርቆሮ አጥር ጨምረውበታል፡፡ በአጥር ለይ አጥር . . .

የሰፈሬን አጠር አጠር ያሉ ክስተቶችን ላስቃኛችሁ . . . በሃገር ሰላም እየሄዳችሁ ድንገት ከፊት ለፊትዎ ወታደራዊ ሰላምታ ገጭ አድርጎልዎት ሊያልፍ ይችላል ወይም ደግሞ   እየተጣደፈ ከፊት ወይ ደግሞ ከበስተኋላ የሚመጣ ጎምላላ “እባክህ/ሽ ራበኝ ጠማኝ ቸገርኝ ሁለተኛ የማልጠይቅህ/ሽ አንድ መቶ ብር ብቻ ስጠኝ/ጪኝ” ሊላችሁ ይችላል፡፡ ሌላም አለ እንዲሁ አገር ሰላም ብላችሁ መንገዳችሁን ይዛችሁ እየሄዳችሁ ነው፤ በእኛ ሰፈር፡፡ ወይ ከፊታችሁ ወይ ደግሞ ከኋላ ከሚሄዱት ሰዎች መካከል በሰላም መንገዱን ይዞ ሲሄድ ያያችሁት ሰው ድንገት የለበሰውን ኮት ወይም ጃኬት አውልቆ ኮሌታውን ይዞ አወናጭፎ እግሩ ላይ ተምትሞ፣ ከራሱ ጋር ወግ ጀምሮ ነጠቅ ነጠቅ እያለ ከኋላ ወደፊት አልፏችሁ፤ ከፊት ለፊታችሁም ከሆነ በድንገት ተስፈንጥሮ ሊሄድ ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ገጠመኝ በእንግድነትዎ ግር ሊልዎት ቢችልም ይህ አይነት ክስተት የሚፈጠረው በመቶ ሰዎች አነስ አድርገነው ሶስት ወይ ሁለት ብቻ ብቻ እንጃ ትክክለኛ ቁጥሩ የማይታወቅ ስለሆነ የእኛን ሰፈር ለመጎብኘት ከተጋበዙ አይፍሩ፡፡ እኔም አሁን ልወደው የማይሞላው ሕይወቴ እዚህ ሰፈር ሲያመጣኝ በመጀመሪያ ሰሞን አስደንብሮኝ ነበር፡፡ ሳጠያይቅ “ኑሮው ነው” አሉኝ፡፡ “ኑሮ እንዴት?” የሚለው የእኔ የመጀመሪያ ጥያቄ ነበር፡፡ ነገሩ የገባኝ ግን ዘግይቶ የአካባቢው የህይወት ሚስጥር ሲገባኝ ነው፡፡

በአዲስ አባበ የጫት መሸጫ እንደ እኛ ሰፈሩ በብዛት ያለበት ያለ አይመስለኝም፡፡ ሳስበው ሳስበው ግን አዲስ አበባ ውስጥ ጫት የማይሸጠው በቤተ እምነቶች እና በጣም ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ብቻ መሰለኝ፤ እዚያም ግን ላለመቃሙ ማረጋገጫ የለኝም፡፡ ድፍን አዲስ አባባ ጫት የመሸጫ ቦታዎች አሏት፤ መቃሚያም እንዲሁ፡፡ የጫት እና የተዛመጅ የስነ ስርአቱን ማስኬጃ የሌለበት አካባቢ ባይኖርም ግን የእኛ ሰፈሩ ግን በብዛቱ ለየት ያለ መስሎኝ ስኮፈስ አንድ ቀን የማይሞላ ሕይወቴ ወደ ለገሃር አካባቢ ወስዶ አይኔ ጉድ አሳየኝ፡፡ የተዛዘሉ፣ ብታይዋቸው ሲያሳዝኑ፣ የተዛዘኑ የጫት መሸጫ ሱቆችን አይቼ፤የኛ ሰፈሮቹን በቃ አበቃላችሁ በቃ አልኳቸው፡፡

የማይሞላ ሕይወትም አይደል ሁልግዜ ጉዞ . . . ከሄድኩበት ስመለስ በእለቱ የነበረችው ፀሐይ ሙሉ ሃይሏን በመጠቀም አምልጣ ነው መሰለኝ አከራረሯ ሌላ ነበር፡፡ በዚህ ድካሜ ታዲያ ታክሲ ውስጥ እንቅልፍ እየከጀለኝ የወንበሩ መደገፊያ ላይ እራሴን አመቻችቼ አስደግፌ ቀጣይ ድካሜ እና የእንቅልፌ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል እየተጠባበቅኩ በነበርኩበት ሁኔታ ባለታክሲው ከፍቶ ይሰማ ከነበረው የኤፍ ኤም ሬዲዮ የሰማሁትን ርዕሰ ጉዳይ እንቅልፌን ባላሰብኩበት ፍጥነት ድራሹን አጠፋው፡፡ የሬዲዮው ፕሮግራም በማህበረሰብ ተኮር ነበር፡፡ ተጋበዡ ሰውዬ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ከአባልነት በዘለለ የሆነ ስልጣን ነገር ያለው የወረዳ ይሁን የክፍለ ከተማ . . . . . . ነው፡፡ ማብራሪያ እየሰጠ ነው፡፡ መሃል ላይ ስለገባሁ መነሻውን ባልይዘውም ቆይታዬ ግን ሁሉንም ነገር ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ

“እኛ የጫት እና የሺሻ ቤቶች የማህብረሰቡ ጠንቅ እንደሆኑ በሚገባ ጠንቅቀን እንረዳለን፣ ከዚህ በፊት ችግሩ ያን ያህል አስቸጋሪ እና የከፋ አልነበረም፡፡ በተወሰነው የማህበረሰቡ ክፍል እና በተወሰነው የሃገሪቱ ክልሎች ብቻ የሚዘወተር በመሆኑ ነበር በይሁንታ ያለፍነው፡፡ አሁን ግን ወደ ሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች እና በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በመስፋፋቱ በተለይ ደግሞ በወጣቱ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ ተዘውታሪ እየሆነ ስለመጣ እና ወጣቱም ወርቃማ ግዜውን እያጠፋበት ስለሆነ ሊገደብ እንደሚገባው በማመን ይህን ስራ ጀምረናል ይላል፡፡ ምን ብላ ጠይቃው ይሆን ወይስ እንደሚወራው “ትልልቆቹ” ያደርጉታል እንደሚባለው ምን ጥያቄ ተፅፎ ተሰጥቷት ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡

ጋዜጠኛዋ ጥያቄዋን ቀጠለች “ይህን ስራ ታዲያ በምን መልኩ ጀመራችሁት እንዴትስ እያስኬዳችሁት ነው?”

“እኛ ይህንን ስራ እየሰራነው ያለነው በየቀበሌዎቹ ውስጥ ካሉ የእድር፣ የማህበር እና የእቁብ ሃለፊዎች ጋራ በጋራ በመግባባት ነው፡፡ አሳታፊ ስራ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ በዚህም ደግሞ ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግበናል፡፡”

“ምንምን?” ብላ በመሃል ብትጠይቅልኝ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ግን ዝም ብላ ለቀቀቸው እሱም ገደብ አልባ፣ መስፈሪያ እና መለኪያ የሌለውን ውጤታማ ያለውን ስራውን፣ ያለገደብ ያለ ከልካይ ለቀቀው፡፡ ደስ ሲል!! በምናባዊ ዓለም በማይጨበጥ ተግባር ሃሳባዊ ስራን እየሰሩ መንሳፈፍ፡፡ ልክ እንደዚህ ነው እንግዲህ ሰውየውም እየተንሳፈፈ የቀጠለው፡፡ አየር ላይ . . .

“በዚህ ስራም የእድር፣ የማህበር እና የእቁብ ድርጅቶች፣ በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለቤቶችን እና አባላቶቻቸውን ይህን ስራ እንዲተዉ እየመከሩ እና እያስተማሩ ነው፡፡ ይህም ውጤታማ በመሆኑም ብዙዎቹ ከዚህ በፊት በዚህ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ስራቸውን እየቀየሩ ነው፡፡ የማይተውትን ደግሞ በደረጃ በደረጃ ከገንዘብ መቀጮ በመጀመር ከአባልነት እስከመሰረዝ የሚደርስ ቅጣት ስለጣሉባቸው ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው፡፡”

እንዴት ነው ግን ይህ ጉዳይ ቀለል ቀጠን አላለም?፡፡ “መኖሪያን፣ የበሰለ እንጀራን እና አዋጭ የሆነ ስራን እንዲህ በቀላሉ ሰዎቹ እንዴት ተዉት?” “የዚህ ጉዳይ ዘለቄታዊ መፍትሄነቱስ እንዴት ይታያል?” “የሰዎቹ ትውውቅስ? አንዱ አንዱን ጋር ባለው ግንኙነት ያለው ይሉኝታስ እንዴት ነው?” ራሴን ጠይቄ መልሱ ግር ቢለኝም፤ ውጤታማነቱ ባይዋጥልኝም ምን ይደረጋል  በሞቅታ፣ በዘመቻ እና በመመሪያ  በሚኖርበት ሃገር ላይ የተባለውን መቀበል ነው እንጂ ለማንስ ይነግሯል? ማንንስ ይጠይቋል? “መልካም፣ ጥሩ ስራ ነው፡፡” በማለት እራሴው መለስኩት፡፡ እንዴት ነው ይህ በቅጣት መልክ የማግለልስ ጉዳይ የማህበረሰቡን መስተጋብር ለረጅም ጊዜ የቆየ አብሮነት ጤናውን አይረብሸውም?  እንደገና ሌላ መድሃኒት እና ሌላ ሐኪም ፍለጋስ አያስኬድምን? በመሃል ተደንቅሬ አናጠብኳችሁ፡፡ ምን ላድረግ በውስጤ የተመላለሱ ጥያቄዎቼ ነበሩ፡፡ ሰውየው አሁንም ገለፃውን ቀጥሏል፡፡ የሰውየው ሃሳብ መጨረሻ ላይ ባይደርስም እኔ ግን የታክሲ ውስጥ ቆይታዬ መጨረሻ እየቀረበ ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የሰማሁትን ላጋራችሁ እና ከመውረጃዬ ስለ ደረስኩ ከታክሲዬ ልውረድ፡፡

“ሴተኛ አዳሪነትም በቀጣይ እቅድ ይዘን የምንሰራበት ጉዳይ ነው” አለ ሰውየው፡፡ “ሴተኛ አዳሪነቱንም ቢሆን እንደጫቱ ሁሉ ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ማህበረሰቡ ትብብር እና ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ እድር፣ እቁብ እና ማህበር የመሳሰሉት የባህል ተቋማት በዚህ ስራ ውስጥ ላሉ እህቶቻችን አማራጭ የስራ መስክ ስለሚያፈላልጉላቸው እና ስለሚፈጥሩላቸው፣ በዚህ ስራ ውስጥም ያሉ እህቶቻችን በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራት ስራቸውን እና ህይወታቸውን የሚቀይሩበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው፡፡” ምን ይሆን የተመቻቸላቸው? ኮብልስቶን ማንጠፍ፣  እንጀራ መጋገር? ወይስ ደግሞ ሌላ ምን ይሆን? ለማንኛውም እ. . . ሰ. . . . ይ. . .  . !!! ብዬ ከታክሲዬ ወረድኩ፡፡